ምርጫ ቦርድ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል ህዝበ ውሳኔን ለማደራጀት 541 ሚሊዮን ብር ያስፈልገኛል አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በደቡብ ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ የሚሆን 541. 2 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገለጸ። ቦርዱ ይህንኑ የበጀት ጥያቄውን ትላንት ማክሰኞ መስከረም 10፤ 2015 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተደንግጓል። ቦርዱ የሚያዘጋጀውን በጀት ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ማጸደቅና እና በስራ ላይ ማዋል እንዳለበትም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። በዚህ መሰረት ተቋሙ፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ክልልን የሚመሰርት ህዝበ ውሳኔ ለማደራጀት የሚያስፈልገውን በጀት ለፓርላማ ማቅረቡ ተነግሯል።

ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን የሚያደራጀው ከአንድ ወር በፊት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 12፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ በደቡብ ክልል የሚገኙት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ያቀረቡትን የጋራ ክልል የመመስረት ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁ ይታወሳል። 

ምክር ቤቱ በዚሁ ጉባኤው፤ ምርጫ ቦርድ አዲሱን ክልል ለመመስረት የሚያስችለውን ሕዝበ ውሳኔ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያደራጅ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ቦርዱ ከአምስት ቀናት በኋላ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ምርጫዎች እና ህዝበ ውሳኔዎች የሚካሄዱበትን የመርኃ ግብር ሰሌዳ የማውጣት ስልጣን “የተቋሙ ብቻ መሆኑን” በወቅቱ አጽንኦት ሰጥቷል። በዚሁ አግባብ የሚያዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳም ወደ ፊት እንደሚገልጽ በዚሁ ደብዳቤው አስታውቆ ነበር። 

ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ “የህዝብ ውሳኔውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ዝርዝር ተግባራትን በማካተት የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅቶ” ለተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጿል። በድርጊት መርኃ ግብር ላይ የተጠቀሱትን አጠቃላይ ተግባራት ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስፈልገው አጠቃላይ የበጀት መጠን ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑን በዚሁ መግለጫው ላይ ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)