በሃሚድ አወል
“ሮሃ ሚዲያ” እና “የአማራ ድምጽ” የተሰኙ የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤቶች በሆኑት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ ክስ ለመመስረት ለዐቃቤ ህግ አምስት ቀናት ተፈቀደ። የክስ መመስረቻ ቀናቱን የፈቀደው ዛሬ ረቡዕ መስከረም 11፤ 2015 የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
ችሎቱ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የፌደራል ፖሊስ “ለመጨረሻ ጊዜ” በተፈቀዱለት አምስት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለመስማት ነበር። ፖሊስ በዛሬው የችሎት ውሎ ምርመራውን አጠናቅቆ ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ገልጿል።
የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ዛሬ አንደደረሰው ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ያረጋገጠው ዐቃቤ ህግ፤ ክስ ለመመስረት ያስችለው ዘንድ 15 ቀናት እንዲሰጡት በጽሁፍ ማመልከቻ አቅርቧል። ዐቃቤ ህግ በዚሁ ማመልከቻው፤ የፌደራል ፖሊስ ባስረከበው የምርመራ መዝገብ ላይ “የወፍ በረር ምልከታ” እንዳደረገ አስታውቋል።
በዚህ ምልከታውም “ምርመራው በቂ ጥርጣሬ እና ደጋፊ ማስረጃዎችን መሰረት አድርጎ የቀረበ መሆኑን” ማረጋገጡንም ለችሎቱ አስረድቷል። ዐቃቤ ህግ ዛሬ እንደደረሰው የገለጸው የፖሊስ የምርመራ መዝገብ፤ ተጠርጣሪዎቹ “የሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ የመከላከያ ሚስጥራዊ ጉዳዮች ለህዝብ ማድረስ፣ እና መከላከያ ሰራዊት የውጊያ ሞራል ለማደብዘዝ ሀሰተኛ ወሬዎችን የመንዛት ወንጀል በመፈጸም” መጠርጠራቸውን እንደሚያትት ገልጿል።
የፌደራል ዐቃቤ ህግ ይህን ቢልም ፖሊስ ጋዜጠኞቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ፊት ባቀረባቸው ወቅት “በሽብር ፈጠራ ወንጀል” እንደጠረጠራቸው አስታውቆ ነበር። ሁለቱ ጋዜጠኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረቡት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ጷጉሜ 4፤ 2014 ነበር።
ዐቃቤ ህግ በዛሬው የችሎት ውሎ የክስ መመስረቻ 15 ቀን እንዲሰጠው የጠየቀው፤ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የተሰበሰበን ማስረጃ “መርምሮ እና ጉዳዮን አገናዝቦ” ክስ ለመመስረት እንደሆነ ገልጿል። ጋዜጠኛ መዓዛ እና ጎበዜን ወክለው በችሎት የተገኙት ሶስት ጠበቆች ይህን የዐቃቤ ህግን ጥያቄ “በጽኑ እንደሚቃወሙ” ለችሎቱ አስታውቀዋል።
የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የዐቃቤ ህግን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ የተጠርጣሪዎችን ዋስትና እንዲያስከብርም የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ጠይቀዋል። ከጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ ጌታነህ፤ ደንበኞቻቸው “የተጠረጠሩት ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ነው። በዚሀ እስከተጠረጠሩ ድረስ ወንጀሉ ዋስትና የሚያስከለክል ስላልሆነ ዋስትና ሊጠበቅላቸው ይገባል” ሲሉ ተከራክረዋል።
ሌላኛው ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁ በበኩላቸው “ተጠርጣሪዎቹ በእስር እንዲቆዩ ተደርጎ ክስ መመስረቻ ቀጠሮ የሚሠጥበት ምክንያት የለም። ከዚህ ችሎት ስልጣንም ውጪ ነው” ሲሉ ችሎቱ የክስ መመስረቻ ጊዜ የመፍቀድ ስልጣን እንደሌለው ተናግረዋል።
አቶ ቤተማርያም አክለውም ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩት በመገናኛ ብዙሃን ፈጸሙት በተባለ ወንጀል መሆኑን አስታውሰው ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ሊታይ ይገባል የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል። ሶስተኛው ጠበቃ አቶ አዲሱ አልጋው ደግሞ “ምርመራው ከተጠናቀቀ በዋስ ቢወጡ ዐቃቤ ህግን ክስ ከመመስረት የሚከለክሉበት አግባብ የለም” ሲሉ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የተነሳውን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል። ዐቃቤ ህግ ተቃውሞውን ያቀረበው በተጠርጣሪዎች ላይ “ተደራራቢ ክስ ሊቀርብ ይችላል” በሚል ምክንያት ነው። ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎች አስተላለፏቸው ባሏቸው “መረጃ፣ የሀሰት ወሬ እና ባወጡት ሚስጥር” ምክንያት “በመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰ ጥቃት እና ያለፈ የሰው ህይወት ሊኖር ይችላል” ብሏል።
ይህን ተከትሎም ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ “የሚፈረድባቸውን ቅጣት በመፍራት ላይመጡ ይችላሉ” የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ገልጿል። ጋዜጠኞቹ “ተደጋጋሚ የጦርነት ውሎዎችን የሚዘግቡ ናቸው” ያለው ዐቃቤ ህግ “ጦርነቱ [አሁንም] የቀጠለ በመሆኑ በዋስትና ቢወጡ ተመሳሳይ የጦርነት ዘገባዎችን ሊሰሩ ስከለሚችሉ ዋስትና ሊከለከሉ ይገባል” ሲል ተከራክሯል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ያነሱት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ አምስት ቀናትን ፈቅዷል። ውጤቱን ለመጠባበቅም ለሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ መስከረም 16፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)