የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሙከራ ምክክር ለማከናወን ቡድኖችን ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊልክ ነው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሙከራ ምክክር ለማድረግ የሚያስችሉ ቡድኖችን በሚቀጥለው ሳምንት ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሊያሰማራ ነው። ኮሚሽኑ መጀመሪያውን ዙር ሀገር አቀፍ ውይይት ከሁለት ወራት በኋላ በህዳር ወር አጋማሽ ላይ የማካሄድ ዕቅድ ይዟል። 

ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፤ ኮሚሽኑ ሀገር አቀፍ ውይይቱን ከመጀመሩ አስቀድሞ “በአነስተኛ ደረጃ ውይይቶችን እያካሄደ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በሶስት ከተሞች ሙከራ ምክክሮች ማድረጉንም ገልጸዋል። የሙከራ ምክክሮቹ የተደረጉት በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ እና በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደዚሁም በአዲስ አበባ ነው።

ዶ/ር ዮናስ ኮሚሽኑ የሙከራ ምክክር ለማድረግ የወሰነበትን ምክንያት ሲያብራሩ “በሁሉም ቦታ አንድ ጊዜ ከመጀመራችን በፊት ወደታች ወርደን፤ አንዱን እንደ ናሙና ወስደን አካሄዳችንን ለማረም፤ ከዚያ ትምህርት እየተማርን እያሻሻልን ለመሄድ ስለፈለግን ነው” ብለዋል። የሙከራ ምክክሩ፤ ኮሚሽኑ በ2015 የመጀመሪያ ወራት ለማካሄድ ያቀዳቸው ውይይቶች አካል መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የ2015 ዕቅድ መሰረት፤ ተቋሙ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር 100 ውይይቶችን ያካሄዳል። ውይይቱ የሚደረገው “በየደረጃው በሚሰበሰቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ” እንደሚሆን በእቅድ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። ኮሚሽኑ እስካሁን የሙከራ ውይይት ባደረገባቸው ከተሞች የሚነሱ አጀንዳዎች “የተለያዩ” እንደነበሩ ከአስራ አንዱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ይገልጻሉ። 

ኮሚሽኑ በጅግጅጋ ባካሄደው ምክክር አብይ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው “ ‘ከመንግስት ምስረታ ጋር በተያያዘ በተለይ ከአድዋ ድል በኋላ እኛ አልተወከልንም’ የሚል ነበር” ሲሉ ዶ/ር ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአዳማ በነበረው ምክክር ደግሞ “ከማንነት ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች” ዋነኞቹ ጉዳዮች እንደነበሩ ጠቁመዋል። 

ተመሳሳይ የሙከራ ምክክሮች ለማድረግ በሚቀጥለው ሳምንት የሚሰማሩት የኮሚሽኑ ቡድኖች፤ “የጸጥታ ስጋት የሌለባቸውን ሁሉንም አካባቢዎች የሚያዳርሱ” እንደሚሆኑ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ አስራ አንዱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች እንደሚካተቱበትም አክለዋል። 

የኮሚሽኑ ቡድኖች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚካሄዱት የሙከራ ምክክሮች ላይ ተገኝተው የአጀንዳ፣ አወያይ እና የምክክር ተሳታፊዎች መረጣ ምን እንደሚመስል ይታዘባሉ። ዶ/ር ዮናስ፤ ቡድኖቹ በሙከራ ምክክሮች ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት ሲያስረዱ “አወያዮቹ እንዴት እንደሚያወያዩ ቁጭ ብለን ማየት አለብን” ይላሉ። 

እነዚህን የሙከራ ምክክሮች የማመቻቸት ሚና ያላቸው “አገናኝ መኮንኖች” መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከዚህ ቀደም ወደ የክልሎቹ በሄዱበት ወቅት፤ ክልሎቹን እና ኮሚሽኑን የማገኛኘት ሚና የሚኖራቸው “አገናኝ መኮንኖች” አዘጋጅተው መመለሳቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ“አገናኝ መኮንኖች” በተጨማሪ ከዞን ጀምሮ እስከ ዋና ጽህፈት ቤት ድረስ ባሉት መዋቅሮቹ 465 የምክክር ሂደት ባለሙያዎችን በተያዘው በጀት ዓመት የመቅጠር ዕቅድ አለው። ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ 94 የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን እንደሚያቋቁም ባለፈው ዓመት ሐምሌ ለፓርላማ ባቀረበው  ዕቅዱ አስታውቆ ነበር።

በእቅዱ መሰረት አስራ ሁለቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሚቋቋሙት በተያዘው መስከረም ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን አለመቋቋሙን ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል። በተመሳሳይ የምክክሩን ተሳታፊዎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና አካላት ለመለየት ለማገዝ ይመለመላሉ የተባሉ 10 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምልመላም አለመከናወኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)