በአማሮ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ 

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ትላንት ረቡዕ መስከረም 11፤ 2015 ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አምስት ሰዎች ተገድለው እና ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ባለስልጣናት እና የሆስፒታል ምንጮች ገለጹ። ጥቃቱን ተከትሎ፤ ከዚህ ቀደም በልዩ ወረዳው በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን መሰል ጥቃቶች ለማጣራት ወደ ስፍራው ያቀኑ የፓርላማ አባላት ያቀዱትን ውይይት ሳያከናውኑ ለመመለስ መገደዳቸውን የልዩ ወረዳው የጸጥታ ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል።

የፓርላማ አባላቱ፤ በልዩ ወረዳው ስር በሚገኘው እና ጥቃት በደረሰበት ዶርባዴ ቀበሌ ትላንት ከሰዓት ከህዝብ ጋር ውይይት የማካሄድ ፕሮግራም ይዘው እንደነበር የአማሮ ልዩ ወረዳ የሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ሰባኪ ሰለሞን ተናግረዋል። የልዩ ወረዳው ፖሊስ አዛዥ ሳጅን አራርሶ ነጋሽ፤ በዶርባዴ ቀበሌ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የፓርላማ አባላቱ የውይይት ቀጠሯቸውን ሰርዘው የአማሮ ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ኬሌ ከተማ መመለሳቸውን ገልጸዋል።    

“የፓርላማ አባላቱ በጀሎ ቀበሌ ያካሄዱትን ውይይትን ጨርሰው ጥቃት ወደተፈጸመበት ቀበሌ መንገድ ላይ ነበሩ። ተኩስ ሲበረታ፣ ሰው ወድቋል ሲባል ወደ ኋላ ተመልሰዋል” ሲሉ የፖሊስ አዛዡ በትላትናው ዕለት የነበረውን ክስተት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። እነዚህ የፓርላማ አባላት ወደ አማሮ ልዩ ወረዳ የተጓዙት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 10፤ 2015 ነበር። 

በቁጥር ሰባት የሆኑት የፓርላማ አባላቱ፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን እንዲያጣራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ያቋቋመው ልዩ ኮሚቴ አባላት ናቸው። ልዩ ኮሚቴው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ካጣራ በኋላ “ለቀጣይ እርምጃዎች የሚረዳ ምክረ ሃሳብ” እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

የፓርላማ አባላቱ በአማሮ ልዩ ወረዳ ቆይታቸው፤ ሁለት ውይይቶችን ማድረጋቸውን አቶ ሰባኪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን የማጣራት ስራ ባስተጓጎለው በትላንቱ ጥቃት፤ በዶርባዴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አምስት ግለሰቦች መገደላቸውን አቶ ካበና ሎሌ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ገልጸዋል። በዚሁ ጥቃት በሶስት ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንም ግለሰቡ አክለዋል። 

የኬሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ናትናኤል ስምዖን፤ በጥቃቱ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ወደ ስፍራው ከተጓዙ የህክምና ባለሙያዎች መስማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው” ያሏቸው ሶስት ግለሰቦችም በሆስፒታሉ ህክምና ማግኘታቸውንም አስረድተዋል። “ግለሰቦቹ በጥይት የተመቱት እግር፣ እጃቸው እና ታፋቸው አካባቢ ነው። ከቁስለኞቹ ቀሪ ሽርፍራፊ ጥይቶችን አውጥተናል” ሲሉ ዶ/ር ናትናኤል በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎችን ጉዳት አብራርተዋል።

የትላንትናውን ጥቃት ያደረሱት “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን፤ ገላና ወረዳ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች” እንደሆኑ በአማሮ ልዩ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አማረ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የታጣቂዎቹ መነሻ የምዕራብ ጉጂ ዞን መሆኑን በተመለከተ የልዩ ወረዳው የሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ሰባኪም ተመሳሳይ መረጃ ሰጥተዋል። ታጣቂዎቹን “ጸረ-ሰላም ኃይሎች” ሲሉ  ከመጥራት በዘለለ ግን ስለማንነታቸው ዝርዝር ገለጻ ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

የአማሮ ልዩ ወረዳ ከኦሮሚያ ክልል በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደምም ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግለት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ በተካሄደ የተወካዮች ምክር ቤት “ልዩ ስብሰባ” ላይ የአማሮ ልዩ ወረዳ የፓርላማ ተወካይ በአካባቢው ላለው ችግር ትኩረት እንዲሰጠው ማሳሰባቸው ይታወሳል። 

የአማሮ ልዩ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የስራ ሂደት አስተባባሪ፤ በልዩ ወረዳው ተከታታይ ጥቃቶች ቢፈጸሙም “ይሄን መጥቶ የሚያስቆም [አካል] የለም” ሲሉ ይከስሳሉ። በልዩ ወረዳው የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል እና የክልሉ ፖሊስ አባላት ቢኖሩም፤ አሁንም ድረስ በአካባቢው “ይህ ነው የሚባል አስተማማኝ ሁኔታ የለም” ይላሉ። “የጸጥታ አካላት ቁጥር አነስተኛ መሆን” እና “ጥቃቱ በሽምቅ የሚፈጸም መሆኑ” ቀድሞ ለመከላከል አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ። 

የትላንቱን ጥቃት በተመለከተ ወደ ስፍራው ያቀኑትን የፓርላማ አባላት ለማነጋገር ሙከራ ብናድርግም፤ “ህጉ አይፈቅድም” በሚል ምክንያት ስለ ክስተቱ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)