ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት ዘጠኝ ግለሰቦች የጠየቁት ዋስትና ውድቅ ተደረገ 

በሃሚድ አወል

ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ከሁለት ቀናት በፊት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ዘጠኝ ተከሳሾች፤ የጠየቁት ዋስትና ውድቅ ተደርጎ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ በተመሳሳይ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው በፖሊስ ላልተያዙ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ የፌደራል ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስ ታዝዟል።

ሁለቱን ትዕዛዞች ያስተላለፈው ዛሬ አርብ መስከረም 13፤ 2015 የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። ችሎቱ ትዕዛዙን የሰጠው የተከሳሾቹን አቆያየት በተመለከተ ትላንት ሐሙስ የግራ ቀኙን አስተያየት ካደመጠ በኋላ ነው። 

ዘጠኙ ተከሳሾች በአንድ ተወካይ ጠበቃ አማካኝነት ለችሎቱ ባቀረቡት አስተያየት ደንበኞቻቸው በዋስትና እንዲወጡ ጠይቀዋል። የጠበቆቹ ተወካይ ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻ ያላቸው እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንም ለዋስትና መጠየቂያ በምክንያትነት አቅርበዋል። ግለሰቦቹ የተከሰሱበት የወንጀል ድንጋጌ ከሰባት እስከ 15 ዓመት እንደሚያስቀጣ የጠቀሱት ጠበቆቹ፤ ቅጣቱ መተርጎም ያለበት “ከመነሻው በመሆኑ” ደንበኞቻቸው ዋስትና ሊፈቅድላቸው ይገባል በሚል ተከራክረዋል።  

በተከሳሽ ጠበቆች የተነሳው የዋስትና ጥያቄ በዐቃቤ ህግ ተቃውሞ ገጥሞታል። ተከሳሾች በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ከተባሉ ከአስር ዓመት በላይ በእስር ሊቀጡ እንደሚችሉ የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ “ዋስትናን በተመለከተ ግልጽ የህግ ክልከላ እያለ ‘መነሻው ነው፤ መድረሻው ነው’ መባል የለበትም” ሲል ተሟግቷል። ስለሆነም ችሎቱ የተከሳሾቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ዐቃቤ ህግ ጠይቋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ “ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የወንጀል የቅጣት ጣሪያ 15 ዓመት በሆነበት፤ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም” ሲል የተካሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል። ችሎቱ ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ እና ላልተያዙ ቀሪ ሁለት ተከሳሾችም የፌደራል ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስ በዛሬው ውሎው አዝዟል። 

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከዚህም በተጨማሪ በ11 ግለሰቦች ላይ የቀረበውን ክስ የመስማት ሂደት፤ በመደበኛው ችሎት ፊት እንዲደረግ ለጥቅምት 3፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። አስራ አንዱ ግለሰቦች፤ በአዲስ አበባ ከተማ ለተገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተደረገው የዕጣ አወጣጥ ተፈጽሟል በተባለ ማጭበርበር ምክንያት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲደረግባቸው የቆዩ ናቸው። 

የፌደራል ዐቃቤ ህግ በአስራ አንዱ ተጠርጣሪዎቹ ላይ “ከባድ የሙስና ወንጀል” በመፈጸም ክስ የመሰረተባቸው ከትላንት በስቲያ ረቡዕ መስከረም 11፤ 2015 ነበር። ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እንዲሁም በቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በኃላፊነት እና በባለሙያነት ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። 

ዐቃቤ ህግ በዚህ የክስ መዝገብ ሶስት ክሶችን አቅርቧል። በሁለት ተደራራቢ ወንጀሎች ክስ የቀረበባቸው፤ በከተማይቱ አስተዳደር ስር ባሉት ሁለቱ ቢሮዎች በሶፍትዌር ፕሮግራመር እና ባለሙያነት ሲሰሩ የነበሩ አምስት ግለሰቦች ናቸው። በሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች በከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ተመድበው ይሰሩ የነበሩ ሶስት ግለሰቦች ላይ የቀረበው “ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም” የሚል ክስ ብቻ ነው። 

ይህ ክስ የሚመለከታቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ምክትላቸው አቶ አብርሃም ሰርሞሎ፤ እንዲሁም የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ኩምሳ ቶላን ነው። ዐቃቤ ህግ በግለሰቦቹ ላይ የመሰረተው ክስ፤ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል” ፈጽመዋል የሚል ነው። 

ዶ/ር ሙሉቀን እና ምክትላቸው አቶ አብርሃም “በስራ ኃላፊነታቸው ሊጠብቁት እና ሊከላከሉት የሚገባውን የመንግስት እና የህዝብ ጥቅም ወደ ጎን በመተው ዕጣው የወጣበት ሲስተም ችግሮች እያሉበት ለዕጣ ማውጣት እንዲውል” በማድረግ መከሰሳቸውን የዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ያሳያል። 

ሶስተኛው ተከሳሽ አቶ ኩምሳ ደግሞ “የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ዳታ እንዳይቀየር መጠበቅ እና መከላከል ሲገባቸው ዳታው ተጋላጭ እንዲሆን በማድረግ፤ ህገ ወጥ ጥቅሞች እና ጉዳት እንዲደርስና እጣውን ለመሰረዝ የሚያበቃ ከፍተኛ ክፍተት እንዲፈጠር” አድርገዋል በሚል በተመሳሳይ በከባድ የሙስና ወንጀል ተከስሰዋል።

ሁለተኛው የዐቃቤ ህግ ክስ የሚመለከተው ደግሞ በሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ከባለሙያ እስከ ዳይሬክተር ኃላፊነት ሲሰሩ በነበሩ ሰባት ግለሰቦች ላይ ነው። ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም” የሚል ነው።

ተከሳሾቹ ለዕጣው ብቁ ያልሆኑ ግለሰቦችን ሐምሌ 1፤ 2014 በወጣው የኮንዶሚኒየም ዕጣ ላይ እንዲካተቱ አደርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ከሰባቱ ተከሳሾች መካከል በክስ ሰነዱ ላይ በአራተኛ ተራ ቁጥር የተመዘገቡት ተከሳሽ አቶ መብራቱ ኪዳነማርያም፤ የ2005 የባለ 3 መኝታ ቤት ተመዝጋቢ ሆነው ሳለ ራሳቸውን ወደ 1997 የባለ 2 መኝታ ተመዝጋቢነት በመቀየር “እጣ ለራሳቸው እንዲወጣላቸው አድርገዋል” በሚል ተከስሰዋል። 

ሰባቱ ተከሳሾች “በጥቅም በመመሳጠር፤ ለዕጣ ብቁ ያልሆኑ ሰዎችን ብቁ እንደሆኑ በማስመሰል እና በእጣው ውስጥ በማካተት፤ አብዛኛዎቹ ዕጣ እንዲወጣላቸው በማድረግ፤ በህዝብና በመንግስት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል” ሲል ዐቃቤ ህግ በመሰረተው ክስ ላይ አትቷል። ዐቃቤ ህግ በዚህኛው ክስ የተካተቱትን ግለሰቦች “ያለ አግባብ” አገኙት ያለውን ጥቅም ለማሳየት የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴያቸውን የሚያሳዩ መረጃዎችን ማያያዙን በሰነድ ማስረጃው ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

በፌደራል ዐቃቤ ህግ የቀረበው ሶስተኛው ክስ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት ቢሮዎች በባለሙያነት እና በሶፍትዌር ፕሮግራመርነት ሲያገለግሉ በነበሩ ስድስት ግለሰቦችን የሚመለከት ነው። ተከሳሾቹ “በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን፤ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። 

ተከሳሾቹ “ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው፤ በስማቸው በከፈቱት የባንክ ሂሳብ እንዲገባ አድርገዋል” ሲል ዐቃቤ ህግ ከስሷቸዋል። ስድስቱ ተከሳሾች፤ ለዕጣው ብቁ ካልሆኑ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለውን ገንዘብ በባንክ ሂሳባቸው መረከባቸውን እና ለሌሎች ግለሰቦች ማስተላለፋቸውን የሚያሳዩ የባንክ ዝውውሮችን ዐቃቤ ህግ በክሱ ሰነዱ ላይ አስፍሯል። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከትላንት በስቲያ በነበረው የችሎት ውሎው፤ ዐቃቤ ህግ በ19 ገጽ ያዘጋጀውን ክስ እና የማስረጃ ዝርዝር ለተከሳሾች እንዲደርሳቸው ተደርጓል። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በአስራ አንዱ ግለሰቦች ላይ ለመሰረተው ክስ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዋን ያስሚን ወሃብረቢን ጨምሮ 15 ምስክሮችን ዘርዝሯል። 

ዐቃቤ ህግ 387 የገጽ ብዛት ያላቸው 29 ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎች እንዳሉትም አመልክቷል። ዐቃቤ ህግ ከጠቀሳቸው የሰነድ ማስረጃዎች መካከል፤ የኮንዶሚኒየም ዕጣው በወጣበት ሶፍትዌር ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሰራቸው ሪፖርቶችም ይገኙበታል። ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ቡና እና አዋሽ ባንኮች ተደርገዋል የተባሉ የገንዘብ ዝውውሮች እና የባንክ ሂሳብ መግለጫዎችም በሰነድ ማስረጃነት ቀርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)