በተስፋለም ወልደየስ
የፌደራል ዐቃቤ ህግ፤ በጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ ክስ የሚመሰርትበት ተጨማሪ አራት ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቀደለት። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ቀናቱን የፈቀደው “ለመጨረሻ ጊዜ” መሆኑን ዛሬ ሰኞ መስከረም 16፤ 2015 በዋለው ችሎት አስታውቋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ትዕዛዙን ያስተላለፈው፤ በዐቃቤ ህግ የቀረበለትን አቤቱታ በቢሮ በኩል ከተመለከተ በኋላ ነው። ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ በጹሁፍ ባስገባው በዚሁ አቤቱታ፤ በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ሲካሄድ የቆየውን የምርመራ መዝገብ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መምሪያ ከተቀበለ በኋላ፤ ክስ ለመመስረት የሚያስችለው 15 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ እንደነበር አስታውሷል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 11 በዋለው ችሎት ግን ክስ ለመመስረቻ የተሰጡት አምስት ቀናት ብቻ እንደነበር ጠቅሷል። ከእነዚህ ቀናት ውስጥ የመንግስት የስራ ቀናት “ሁለት ብቻ” እንደሆኑ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ዐቃቤ ህግ፤ እነዚህ ቀናት አጭር በመሆናቸው “በምርመራ መዝገቡ ላይ ውሳኔ ለመስጠት በቂ ጊዜ አላገኘንም” ብሏል። በዚህም ምክንያት ክስ ለመመስረቻ ተጨማሪ 10 ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የዐቃቤ ህግ አቤቱታ በዳኞች ፊት እንዲደርሳቸው የተደረጉት ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆቻቸው፤ አጭር ምክክር ካደረጉ በኋላ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። ዛሬ በችሎት ከተገኙት ሶስት ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ ጌታነህ፤ “ተጠርጣሪዎቹ በእስር የሚቆዩት የምርመራ ሂደቱን ምቹ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን” ጠቅሰው፤ የእዚህ ምክንያቱ ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ “ማስረጃ ሊያጠፉ፣ ሊያበላሹ ወይም ሊያሸሹ ይችላሉ” ስለሚባል እንደሆነ አመልክተዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲደረግ የነበረው ምርመራ ተጠናቅቆ፤ የምርመራ መዝገቡ ለዐቃቤ ህግ ከተላለፈ በኋላ ግን ተጠርጣሪዎቹ “የሚያበላሹት፣ የሚያጠፉት ወይም የሚያሸሹት መረጃ የለም” ሲሉ ተከራክረዋል። የዐቃቤ ህግ ክስ መመስረት እና የደንበኞቻቸው “በእስር መቆየት ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም” ያሉት ጠበቃው፤ ደንበኞቻቸው በዋስትና ከተለቀቁ በኋላ ዐቃቤ ህግ “አስፈላጊ ባለው ሰዓት ወይንም ዝግጅቱን በጨረሰ ጊዜ” ክስ መመስረት እንደሚችል አስረድተዋል።
ጠበቃ አዲሱ ከዚህ በተጨማሪም “መጀመሪያውኑም ቢሆን ለዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ ቀናት ሊሰጠው አይገባም ነበር” ሲሉ ባለፈው ሳምንት በችሎቱ የተላለፈውን ትዕዛዝ ሞግተዋል። ዐቃቤ ህግ ባለፈው ችሎት 15 የክስ መመስረቻ ቀናትን በጠየቀበት ወቅት፤ የምርመራ መዝገቡን መመልከቱን እና “ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ምልክቶች አግኝቼያለሁ” ማለቱን ለፍርድ ቤት ያስታወሱት ጠበቃው፤ አሁን ተመልሶ “መዝገቡን እየመረመርኩ ነው” ማለቱን ተቃውመዋል።
በቢሮ ከተሰየሙት ሁለት ዳኞች መካከል አንደኛው፤ ለዐቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም ክስ ለመመስረቻ ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜ ምን ያህል እንደነበር ጠይቀዋል። ለዐቃቤ ህግ ተፈቅዶ የነበረው አምስት ቀን እንደነበር ከተረዱ በኋላ፤ ዐቃቤ በተሰጠው ጊዜ ለምን ክስ መመስረት እንዳልቻለ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርበዋል።
ዐቃቤ ህግ ለጥያቄው በሰጠው ምላሽ፤ በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ላይ የቀረበን አንድ የቪዲዮ ማስረጃ ብቻ ለመመልከት ሶስት ሰዓት ገደማ እንደወሰደ በምሳሌነት አንስቷል። በዚህ አይነት ለክሱ የሚቀርቡ ሌሎችንም ማስረጃዎች ተመልክቶ ክስ ለመመስረት ሁለት የስራ ቀናት በቂ አለመሆናቸውንም ለዳኛው አስረድቷል።
ይህ ጉዳይ ሚዲያዎች የሚከታተሉት እና በልዩ ትኩረት እየተሰራ ያለ መሆኑን ዐቃቤ ህግ በሚያብራራበት ወቅት፤ ጥያቄውን ያቀረቡት ዳኛ ንግግሩን አቋርጠው “ይህን ጉዳይ ከሌላ ጉዳይ የተለየ አድርገን አናየውም” ብለዋል። “አንድ ጉዳይ በጣም rush ሲደረግ በፍትህ ላይ ስህተት ይፈጠራል” በማለት ዐቃቤ ህግ ያቀረበው አገላለጽም ዳኛውን አስቆጥቷል። ዐቃቤ ህግ ሌሎች አላስፈላጊ ገለጻዎችን በመተው ክስ ለመመስረት ያልቻለበትን ምክንያት ብቻ እንዲያስረዳም በተግሳጽ መልክ አሳስበዋል።
ዐቃቤ ህግ በድጋሚ የተሰጡት ሁለት ቀናት አጭር መሆናቸውን በመከራከሪያነት አንስቷል። “የምንችለውን ጥረት አድርገናል። በሁለት የመንግስት የስራ ቀናት ግን ክስ መመስረት አልቻልንም” ሲል ለዳኛው አስረድቷል።
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በሌላ መዝገብ ጉዳዩ እየታየ ካለው ተጠርጣሪ አሳዬ ደርቤ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ በማስረጃነት መያዙን የገለጸው ዐቃቤ ህግ፤ በሌላኛው ተጠርጣሪ ላይ ሲካሄድ የነበረው ምርመራ ተጠናቅቆ መዝገቡ የደረሰው ዛሬ መሆኑንም አብራርቷል። ጉዳዩ በሁለት መዝገብ ተከፍሎ መቅረቡን የገለጸው ዐቃቤ ህግ፤ በአንድ መዝገብ ለማድረግ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለችሎቱ ገልጿል።
ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ ለዐቃቤ ህግ ማብራሪያ በሰጡት ምላሽ፤ የእነዚህ ተጠርጣሪዎች በእስር መቆየት፣ አለመቆየት ከሌላ መዝገብ ጋር ሊያያዝ አይገባውም ብለዋል። ዐቃቤ ህግ በሁለተኛ ተጠርጣሪ ጎበዜ ሲሳይ ላይ የጠቀሰው ጉዳይ ለአንደኛዋ ተጠርጣሪ መዓዛ መሐመድ በእስር መቆየት ምክንያት ሊሆን እንደማይገባም ተከራክረዋል። ዐቃቤ ህግ “የሌላ ተጠርጣሪ ጉዳይን ማምጣቱ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም” ሲሉም አክለዋል።
ሌላኛው ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁ በበኩላቸው የህግ መከራከሪያዎችን በማንሳት የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል። ጠበቃ ቤተማርያም በመጀመሪያ ያቀረቡት የህግ መከራከሪያ፤ በወንጀል የሚጠረጠሩ ጋዜጠኞችን በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ የተቀመጠውን አንቀጽ ነው።
ጠበቃው የጠቀሱት የአዋጁ ድንጋጌ “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት” ይላል። አዋጁ በምርመራ ጊዜ የጋዜጠኞችን እስር ያስወገደ በመሆኑ፤ ደንበኞቻቸው በእስር መቆየት እንደሌለባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጡት ሁለት ዳኞች፤ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ከመስጠታቸው በፊት ዐቃቤ ህግ፣ ጠበቆች እና ተከሳሾች ከቢሮ ውጭ እንዲቆዩ በማድረግ ለደቂቃዎች ምክክር አድርገዋል። ዐቃቤ ህግ ክሱን ለማቅረብ ሁለት ቀናት ብቻ እንደነበሩት ከግምት ውስጥ ማስገባታቸውን የገለጹት ዳኞች፤ ክስ ለመመስረቻ ተጨማሪ ቀናት መስጠት “አስፈላጊ ሆኖ” በማግኘታቸው ለመጨረሻ ጊዜ አራት ቀናት መፍቀዳቸውን አስታውቀዋል። የዐቃቤ ህግን ክስ ለመጠባበቅም ለመጪው አርብ መስከረም 20 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለዋል]