የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ አዲሱ “የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ ስርዓት መመሪያ” ምን አይነት ገደቦችን በውስጡ ይዟል?  

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ለ2015 በጀት ዓመት ጥብቅ “የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ ስርዓት መመሪያ” ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል። በክልሉ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ የጸደቀው ይህ መመሪያ፤ በደመወዝ አከፋፈል፣ በሰራተኛ ቅጥር፣ ለመንግስት ሰራተኞች በሚሰጥ የትምህርት ዕድል ላይ ብርቱ ቁጥጥር የሚያደርግ ነው። 

በዚሁ የክልሉ መመሪያ ላይ፤ የቢሮ ኪራይ፣ የቋሚ እና አላቂ ዕቃዎች ግዢ፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ላፕቶፖች፣ ሞተር ሳይክሎች ግዢ እና የጨረታ ሂደት ላይ የተደረጉ ገደቦች ተካትተዋል። አዲሱ መመሪያ፤ የክልሉ መስሪያ ቤቶች ከተመደበላቸው በጀት በላይ “ወጪ ማድረግን ወይም በጀት ሳይጸድቅ በታሳቢ እየተባለ ከፍተኛ ወጪ” ማውጣትን ይከለክላል። 

በመመሪያው መሰረት፤ የክልሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች “የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በራስ ተቋም ብቻ በማጽደቅ ክፍያ መፈጸም” አይችሉም። መስሪያ ቤቶቹ “ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅምን” በተመለከተ ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አቅርበው በካቢኔ ካልጸደቀላቸው በስተቀር፤ ከዚህ ቀደም እንደነበረው “በሰርኩላር በተዋረድ ማስተላለፍ” እንደማይፈቅድላቸው በመመሪያው ተቀምጧል።

በ14 ገጾች የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ በጥቅማ ጥቅም ክፍያዎች፣ በተሽከርካሪዎች አጠቃቀም እና ጥገና እንዲሁም በነዳጅ እና ቅባት አጠቃቀም ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ እርምጃዎችን ዘርዝሯል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ለስልጠና እና የመስክ ስራ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ተሽከርካሪዎችን “በተናጠል ሳይሆን ስራዎችን በማቀናጀት እና በማስተባበር በቅንጅት መጠቀም” እንዳለባቸው የሚያሳስበው መመሪያው፤ ለስራ ኃላፊዎች የሚፈቀደውን የነዳጅ ፍጆታ መጠንም በሊትር ገድቧል።  

የክልሉ ኮር አመራሮች፣ የጸጥታ እና የፖሊስ ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች፤ በከተማ ውስጥ ለሚኖራቸው እንቅስቃሴ እስከ 150 ሊትር ነዳጅ እንዲጠቀሙ በመመሪያው ተፈቅዶላቸዋል። ሌሎች የበላይ ኃላፊዎች ለሚያደርጓቸው ተመሳሳይ ጉዞዎች በወር 70 ሊትር ነዳጅ መፈቀዱን የሚገልጸው መመሪያው፤ ከዚያ በላይ ለሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ኃላፊዎች ወጪውን ራሳቸው እንደሚሸፍኑ ደንግጓል።

ከመስከረም 4፤ 2015 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ በተነገረለት በዚህ መመሪያ፤ በክልሉ የሚካሄዱ ስብሰባዎች እና ስልጠናዎችን በተመለከተም ገደቦች ተቀምጠዋል። ስብሰባዎችን እና ስልጠናዎችን ለማካሄድ ለአዳራሽ ኪራይ የሚወጣ ክፍያ ለማስቀረት፤ የክልሉ መስሪያ ቤቶች በመንግስት ተቋማት አዳራሾች እንዲጠቀሙ መመሪያው አዝዟል። በመደበኛ በጀትም ሆነ ከልማት አጋሮች ወይም ባለድርሻ አካላት ጋር ለሚካሄዱ ስብሰባዎች እና ክብረ በዓል ተሳታፊዎች፤ ቦርሳ፣ ቲ ሸርት፣ ኮፊያ እና ሻርፕ መግዛትም በመመሪያው ተከልክሏል።

በርከት ያሉ የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ እርምጃዎች የተካተቱበት ይህን መመሪያ በተመለከተ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ ጋር በስልክ ቆይታ አድርጓል። ሙሉ ቃለ ምልልሱ እንደሚከተለው ቀርቧል። 


ጥያቄ፡- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ2015 በጀት ዓመት፤ “ልዩ የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ ስርዓት መመሪያ” አውጥቷል። መመሪያውን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

አቶ ዚያድ፡- ከአጠቃላይ ወጪ እና ካለን ልማት ፍላጎት አኳያ በየጊዜው የሚደረገው የበጀት ጭማሬው አነስተኛ ነው። ዘንድሮም እንደ ክልል፤ [በጀታችን] ጭማሬ ያለው ከ10 እስከ 11 በመቶ ብቻ ነው። ስለዚህ ያለን አማራጭ አንደኛ ሀብት መፍጠር፣ ሁለተኛ ደግሞ ያለንን ሀብት በቁጠባ መጠቀም ነው። በመሆኑም ወጪ ቅነሳ መመሪያ አዘጋጅተናል። መደበኛ ህጎቻችን እንዳሉ ሆነው ነገር ግን በተለየ መልኩ ገደብ መጣል አለበት ብለን ወስነናል። ከንብረት [አስተዳደር] እስከ አመራር ጥቅማ ጥቅም እና ሌሎች የግዢ ስርዓቶቻችንም፤ ወጪ ቆጣቢ እና ሀብትን በሚፈጥር አኳኋን መስራት አለበት ብለን ነው ገደቦችን የጣልነው።

ጥያቄ፡- የክልሉ የወጪ ቅነሳ መመሪያ ለ2015 በጀት ዓመት የወጣ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። መመሪያው ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ ከዚህ በጀት ዓመት ጋር አብሮ ይጠናቀቃል ወይስ ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል?

አቶ ዚያድ፡- ተፈጸሚነቱ ለበጀት ዓመቱ ሆኖ የሚሻሻሉ ነገሮች እየተሻሻሉ እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀጥል ይሆናል።

ጥያቄ፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት፤ ከግዢ፣ ከቢሮ ኪራይ እንዲሁም ከተሽከርካሪ አጠቃቀም እና ጥገና ጋር በተያያዘ ብዙ ወጪዎች እንዳሉበት በመመሪያው ተገልጿል። ከእነዚህን ወጪዎች ጋር በተያያዘ የነበረው የበጀት አጠቃቀም፤ ክፍተቶች ነበሩበት? ይህ መመሪያስ ምን አይነት ገደቦችን እና ክልከላዎችን ነው ያደረገው? 

አቶ ዚያድ፡- በአመራር ደረጃ፤ አንዱ ከፍተኛ ወጪ የምናወጣው ለነዳጅ ነው። አመራሩ ያለገደብ ነበር ነዳጅ በወር የሚጠቀመው። በክልላችን አንድ መኪና መስክ እንኳን ሳይሄድ እዚህ [ከተማ] ዙሪያ ላይ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ብቻ በወር ከ200 እስከ 300 [ሊትር] ድረስ ይጠቀማል። አሁን ኮር አመራሮችን ሳይጨምር “ከ70 ሊትር በላይ መጠቀም አይቻልም” የሚለው አንዱ ገደብ የጣልንበት ጉዳይ ነው።

ሌላው luxury [ቅንጡ] ላፕቶፕ እና የሞባይሎች ስልክ አንዳንድ ጊዜ ይገዛሉ። ከሌሎች ክልሎች ጋር ስናነጻጽረው ብዙም የተጋነነ ነው ባይባልም፤ በእኛ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ ለአንድ ሞባይል ከ70 እስከ 80 ሺህ ብር ድረስ  ይወጣል። በዚህ ዓመት ይህን በሙሉ ለልማት ለማዋል ሲባል፤ ምንም አይነት የላፕቶፕም ሆነ የሞባይል ግዢ ለየትኛውም አመራር መግዛት እንደማይቻልና በራሱ ገንዘብ እንዲገዛ የሚል ነው አንዱ መመሪያው ላይ ያስቀመጥነው። አዲስ አመራር ተሹሞ ከመጣ እና ምናልባትም በተለየ መልኩ መገዛት ካለበት ተፈቅዶ ይገዛል።

መኪና ጥገና ላይም ዝም ብሎ ያለ ውድድር በቀጥታ በተለያዩ ኩባንያዎች እና የግል ጋራጆች ገብተው የሚጠገኑበት ሁኔታ ነበር። ከዚህም ጋር ተያይዞ የክልሉ ጋራጅ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባ እያደረግን ነው። የክልሉ የገጠር መንገዶች ባለስልጣን የሚባል ጋራጅ አለ። እሱን እስከ መስከረም 30 ወደ ስራ አስገብተን፤ አብዛኛው [የተሽከርካሪ] ጥገና በመንግስት፤ ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ ይደረጋል። ከፍ ከፍ ያሉትን እና ሞተራቸው ውስብስብ የሆኑትን “በሞኢንኮ” ማስጠገን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከጋራጁ [አቅም] በላይ የሚሆኑ ካሉ ደግሞ በቀጥታ መግባታቸው ቀርቶ በውድድር ብቻ በመንግስት አሠራር ይከናወናል።

ሌላው እንደኛ ክልል፤ አላቂ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ወጪ እናወጣለን። እዚያ አካባቢም ገደብ ጥለናል። ግንባታዎች አካባቢም ሆን ብሎ ግንባታን ማጓተት ይስተዋላል። ግንባታዎችን አጓትቶ፤ የጊዜም ሆነ የጥራት እንዲሁም የበጀት ጉድለት የሚያስከትሉ ኃላፊዎችም ሆኑ የስራ ክፍሎች [ላይ] እስካሁን ድረስ ተጠያቂነት የሚያስከትል አሰራር አልነበረም። አሁን ግን ህጋዊም ሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ መመሪያችን ላይ አመላክተናል።

ለጨረታ ተብሎ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ [የሚደረጉ] መመላለሶች ነበሩ። እንደምታውቀው በኮሚቴ ነው ግዢ የሚፈጸመው። የጨረታ ኮሚቴ የሚባል አለ። አዲስ አበባ ላይ ብዙ ተጽዕኖ ላይፈጥር ይችላል። እንደኛ ክልል ግን ከአንድ ቢሮ ብቻ ከ10 ያላነሰ ሰው በዓመት ቢያንስ ሁለት እና ሶስት ጊዜ ይመላለሳል። ከአሁን በኋላ ባሉት የጨረታ ሂደቶች ለጨረታ አዲስ አበባ መሄድ ቀርቶ አሶሳ በክልል ማዕከል ብቻ ይከናወናል።

ሌሎችም በርካታ ለአብነት የምናነሳቸው ነገሮች አሉ “ገደብ ይጣልባቸው” ብለን የወሰንናቸው። ለምሳሌ ጎማ ግዢን ብትመለከት፤ የፈለገ ሰው በዓመት ሶስትም አራትም ጊዜ ጎማ ይቀይራል። በዚህኛው [መመሪያ] ግን ከጸጥታ ኃላፊዎች እና ከስራ ባህሪያቸው አኳያ ከሚፈቀድላቸው በስተቀር፤ ማንኛውም ቢሮ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ጎማ መቀየር አይችልም።

የቢሮ ኪራይን በተመለከተ እንደሌሎች ክልሎች ባይበዛም እኛ ጋርም ቢሮ ኪራዮች አሉ። በእኛ ዳሰሳ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ በዓመት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል። ያለችንን በጀት ማትረፍ ስለሚያስፈልግ ከዚህ በኋላ፤ አንደኛ በተቀናጀ አኳኋን ቢሮዎችን የምንጠቀምበት፤ ሁለተኛ ደግሞ አነስተኛ ወጪ የሚያወጡ ቢሮዎችን የምንከራይበት ስርዓት ይዘረጋል።

የመስክ ስራዎች፣ የጋራ መድረኮች እና ስልጠናዎች ከአሁን በኋላ በተቀናጀ መልኩ ሰብሰብ ተደርገው በክላስተር የሚመሩበት፤ ጉዞዎች በክላስተር የሚደረጉበት አሰራር ይኖራል። እነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች ናቸው ገደብ የተጣለባቸው እና በተወሰነ ደረጃ [ወጪ] ሊቆጥቡ ይችላሉ ያልናቸው። ማንኛውም የተጋነነ ወጪ መከልከል አለበት። ይህን ደግሞ የክልሉ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ቢሮ እና ኦዲት መስሪያ ቤት ክትትል እያደረጉ በየሶስት ወሩ ለካቢኔው ሪፖርት ያቀርባሉ።

ጥያቄ፦ በአዲሱ መመሪያ፤ አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር የአዲስ እና የኮንትራት ሰራተኞች ቅጥር እንዲቆም ተደርጓል። የክልሉ የሰው ኃይል ቅጥር ሁኔታ ምን ይመስላል?  አዲስ ቅጥር መቆሙ ወጪን ምን ያህል ይቆጥባል?

አቶ ዚያድ፡- እስካሁን የነበረን ልቅ የሆነ የሰራተኛ ቅጥር ነው። አሁን ባለን ግምገማ እኛ እንደ ክልል፤ የሰራተኛው ብዛት ከህዝቡ ቁጥር ጋር ስታነጻጽረው በratio ከፍተኛ ቁጥር የሚይዝ ነው። አሁን ባለን በዚህ ዓመት እንኳን ደመወዝ የደለደልነው ከ48 ሺህ በላይ ሰራተኛ ነው በእኛ ክልል ያለው። ይሄ ከ1.2 እስከ 1.3 ሚሊዮን ህዝብ ላለበት ክልል በratio ስታካፍለው፤ ለአንድ ሰራተኛ ምን ያህል ህዝብ ነው ያለው ብለህ ስታመጣው፤ በጣም ከፍተኛ ratio ነው። ከፍተኛነቱ በዓለም አቀፍም፣ በሀገር አቀፍም፣ በሌሎች ክልሎች ደረጃም ነው። ከፍተኛ የሰራተኛ ክምችት እንዳለ ነው የሚያሳየው። 

በተለያየ ጊዜ የምናደርጋቸው ግምገማዎች እና የምናቀርባቸው መረጃዎች የሚያሳዩት፤ ከልማት ይልቅ ሰራተኛ ቅጥር ላይ ከፍተኛ በጀት እንደምንወስድ ነው። ስለሆነም ከአሁን በኋላ አስገዳጅ በሆነ አግባብ፤ ተቋም ተከፍቶ ተጨማሪ ወረዳዎች ሲጨምሩ የሚቀጠሩ ካልሆነ በስተቀር፤ የሰራተኛ ቅጥር ማድረጉ የሚመከር አይደለም። ለልማት የምናውለውን consume እያደረገብን ነው። 

ለምሳሌ ወረዳዎች ብትወስድ በአማካኝ እስከ 85 በመቶ በጀታቸውን ደመወዝ ነው የሚከፍሉት። በክልል [ደረጃ] ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሰራተኛ ደመወዝ ይወስደዋል። የክልል ሴክተሮች እና ዞን ማለት ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው በጀት ለካፒታል ከመዋል ይልቅ፤ ለደመወዝ እና ስራ ማስኬጃ ላይ እየዋለ ስለሆነ የሰው ኃይል ቅጥሩን ከአሁን በኋላ discourage እያደረግን የምንሄድበት ስርዓት መዘርጋት አለበት። በቀጣይ ደግሞ ጥናትን መሰረት አድርጎ ተቋምን መልሶ revise እስከ ማድረግ ድረስ መሄድ አለባቸው።

የሰራተኛ ቁጥሩ፤ ቢያንስ በዓመት እስከ 5 ሺህ፣ እስከ 6 ሺህ  ይቀጠራል። ዓምና በሰርኩላርን በትነን፣ ገደብ ጥለንበት በአንድ ዓመት ብቻ የተቀጠረው 2,600 ነው። የሰራተኛ ቅጥሩ ገደብ የተጣለበት፤ እርሱ አካባቢ “manage ማድረግ ወሳኝ ነው” ብለን ስላሰብን ነው። 

ጥያቄ፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት የበጀት እጥረት እንዳጋጠመው በመመሪያው ላይ ተጠቅሷል። በእነዚህ ዓመታት ክልሉ ያጋጠመው የበጀት እጥረት ምን ያህል ነበር? ለበጀት እጥረቱ ምክንያቱስ ምንድን ነው?

አቶ ዚያድ፡- እጥረቱ [ያጋጠመው] በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛ በ2009 ዓ.ም እንደ ፌደራል የተደረገው የቀመር ክፍፍል አለ። እኛ በአጠቃላይ ለክልሎች ሲመደብ ከነበረው፤ ከሁለት በመቶ በላይ እናገኝ ነበር። እሱ ወደ 1.83 በመቶ ዝቅ ተደርጓል። አሁን ክልሎች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር ደግሞ 1.8 በመቶ ገደማ ነው የምናገኘው። ስለዚህ በ2010 ዓ.ም. በተከለሰው ቀመር 0.2 በመቶ ተቀንሶብናል። አንደኛ እሱ ጫና ነበረው። 

ቢያንስ በዓመት ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ከሚመደብልን ቀንሷል በየዓመቱ እያደገ መሄድ ሲገባው። ለምሳሌ በ2010 ዓ.ም. የተመደበልንን በጀት ብትወስድ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ነው የቀነሰው። ይሄ አንዱ ምክንያት ነው። ሁለተኛው የህዝብ መልማት ፍላጎት ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር በጀቱ በዚያው ልክ ከፍ እያለ አይደለም። አንደኛ የፌደራሉ በመቀነሱ፤ ሁለተኛ ደግሞ አካባቢው ላይ የጸጥታ ችግሮች በመኖራቸው፤ ኢንቨስትመንት ትንሽ የተስተጓጎለባቸው አካባቢዎች አሉ። የሚሰበሰበው ገቢ፤ ማደግ በሚገባው ፍጥነት እያደገ አይደለም። 

የተወሰኑ ዞኖቻችን፣ ወረዳዎቻችን የጸጥታ ችግር ውስጥ ነበሩ። ያ በምንፈልገው ልክ ገቢ እንዳንሰበስብ አድርጎናል። አጠቃላይ በጀቱ ባይቀንስም፤ በዓመት የጭማሪው ጭማሪ እየቀነሰ ነው የሄደው። የእኛ በጀት በዓመት እስከ 30 በመቶ ይጨምር ነበር። አሁን ከሁለት ዲጂት በታች ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዓመት 10 እና 11 በመቶ ይጨምራል። ለምሳሌ በዚህ ዓመት የክልሎች [በጀት] ሲጨምር፤ የእኛ የፌደራል በጀት ጭማሪ የነበረው አራት በመቶ ብቻ ነው። 

ጥያቄ፦ ባለፉት ሶስት ዓመታት ክልሉ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት የተስተጓጎሉ ፕሮጀክቶች ወይም ስራዎች አሉ?

አቶ ዚያድ፡- በአጠቃላይ የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች ለማስጨረስ በጣም አዳጋች ሆኖብን ነበር። የጀመርናቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ። የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ የራሱ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም፤ ነገር ግን ዋነኛው የበጀት እጥረት ነው። ለምሳሌ በ2009 እና በ2010 የያዝናቸው፤ በአንድ ዓመት የምንጨርሳቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች ነበሩ። [የክልሉ በጀት] በአንድ ጊዜ ከነበረበት በ300 ሚሊዮን ብር ገደማ ሲቀንስ፤ ለካፒታል [ወጪ] የያዝከውን እንዳለ ወደ አስተዳደራዊ ወጪ አምጥተህ ነው የምትጠቀመው። ይህ በዋናነት የምንሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል። በዋናነት ከካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ በጀት እንዲቀነስ አድርጓል። ፕሮጀክቶች ጊዜ በመውሰዳቸው ተጨማሪ በጀት፣ ተጨማሪ ጊዜ እንዲጠይቁ አድርጓል። በምንፈልገው ደረጃ መንግስታዊ አገልግሎቶች ወደ ስራ በማስገባት ላይ የራሱ ተጽዕኖ አለው። የበጀት እጥረቱ እስከ ወረዳ ድረስ ሴክተሮች በሚፈለገው ደረጃ ስራ እንዳይሰሩ አድርጓል።

ጥያቄ፦ አዲሱ መመሪያ እነዚህን ችግሮች ይቀርፋል ብለው ያምናሉ?

አቶ ዚያድ አብዱላሂ፡- መቶ ፐርሰንት እሱ ብቻ ይፈታል ብለን እምነት የለንም። ገቢ ማሳደግ ላይ ትኩረት እያደረግን ነው። ለምሳሌ አንጻራዊ ሰላም የመጣባቸው አካባቢዎች አሉ። መተከል [ዞን] ከፍተኛ ኢንቬስተር የሚንቀሳቀስበት አካባቢ ነው። ከህዳሴው ግድብ ጋርም ተያይዞ የሚፈጠሩ ተጨማሪ ገቢዎች አሉ። እርሱ አንዱ ተስፋ የምንጥልበት ነው። በእርሱ የተሻለ ገቢ እንሰበስባለን የሚል እምነት አለን።

ሌላው ደግሞ ያለችንን ውስን ሀብት በአግባቡ ቆጥበን ከተጠቀምን፤ ቢያንስ ባለችን ውስን ሀብት ዓመቱን መሸፈን እንችላለን። በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ፤ አንዳንድ ጊዜ ዓመቱን መሸፈን አንችልም። በብድር ከፌደራል እየወሰድን ጭምር መደበኛ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል የምናደርገው ጥረት ነበር። በዚህ ዓመት ግን በሶስት ዓመት የወሰድናቸውን በከፊል እንከፍል እንጂ፤ በዚህ ዓመት ብድር መውሰድ የለብንም የሚል አቋም ተይዟል። እየከፈልን፤ ተጨማሪ እዳ ወደ ክልሉ እንዳይመጣ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን። ስለዚህ ወጪ ከተቆጠበ፤ ባለን በጀት ዓመቱን በሙሉ መዝለቅ የምንችልበት እና ደመወዝ ሳይጎድል የምንከፍልበት ሁኔታ እንፈጥራለን ብለን እናስባለን። 

ጥያቄ፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፌደራል መንግስት የተበደረው ገንዘብ ምን ያህል ነው?

አቶ ዚያድ አብዱላሂ፡- አሁን እስከ 500 ሚሊዮን ብር ብድር አለብን። አንድ ሶስተኛውን በዚህ ዓመት እንመልሳለን፡፡

ጥያቄ፦ የክልሉ መንግስት አዲስ ያወጣውን የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል ዝግጁ ነው?

አቶ ዚያድ አብዱላሂ፡- ዝግጁነቱ ምንም ጥርጥር የለውም። መመሪያው የወጣው በካቢኔ ደረጃ ነው። እስካሁን ድረስ ወጪ እና ንብረቶች ላይ ጥሰቶች ሲገኙ፤ መመሪያ አውጥቶ ገደብ መጣል የክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊነት ነበር። ነገር ግን ደረጃውን ከፍ ስናደርገው፤ ይበልጥ ተቀባይነት ለማግኘት እና ሶስቱም የክልሉ የመንግስት አካላት ማለትም የህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚው እና ህግ አስፈጻሚው ሊተገብረው በሚችለው አግባብ ነው [መመሪያውን] በክልሉ ካቢኔ ያወጣነው። መመሪያው የወጣው፤ በሰርኩላር የምታደርጉትን በመመሪያ ደረጃ ይሁን የሚል አቋም ተወስዶ ነው። የክልሉ ርዕስ መስተዳድር [አቶ አሻድሊ ሀሰን] የመመሪያው አተገባበር ላይ ክትትል ስለሚያደርጉ፤ እኛም እያንዳንዷን ነገር እየተከታተልን [ለካቢኔው] ስለምናቀርብ ይተገበራል ብለን እናስባለን። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)