በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ የንግድ ባንኮች ተበዳሪዎች በሚያቀርቧቸው ኦዲት የተደረጉ የሂሳብ መግለጫዎች ላይ ተገቢውን ማጣራት እንዲያከናውኑ አሳሰበ። ብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ ለባንኮች የሚቀርቡ “ሀሰተኛ የሆኑ የኦዲት ሪፖርቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል” በሚል ነው።
የባንኮች እና ሌሎች የገንዘብ ተቋማትን ስራዎች የመቆጣጠር ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ይህንኑ ማሳሰቢያ የያዘ ደብዳቤ ከሁለት ሳምንት በፊት መስከረም 5፤ 2015 ለሁሉም የንግድ ባንኮች አሰራጭቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኪንግ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር ፊርማን የያዘው ይኸው ደብዳቤ፤ ከባንክ ብድር የሚወስዱ የተወሰኑ ደንበኞች የሚያቀርቧቸው የኦዲት ሪፖርቶች ሀሰተኛ መሆናቸውን መረዳቱን ገልጿል።
የተወሰኑ የባንክ ደንበኞች በሚያቀርቧቸው የኦዲት ሪፖርቶች ደግሞ፤ የሂሳብ ምርመራ ማድረግ የተፈቀደላቸው ኦዲተሮች ስም ያለ እነርሱ እውቅና በሀሰት ተጠቅሶ መገኘቱን ብሔራዊ ባንክ ገልጿል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ኦዲት የተደረገ የሂሳብ መግለጫ ባንኮች ከደንበኞቻቸው የብድር ጥያቄ ሲቀርብላቸው ከሚመለከቷቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ ነው።
አሁን በስራ ላይ ላሉ 30 ባንኮች በሰርኩላር መልክ በተላለፈው የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ ላይም፤ ባንኮች ብድር ለመስጠት ከመወሰናቸው በፊት የተበዳሪዎችን ብቁነት እና የመክፈል አቅምን በተመለከተ “ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ” የሂሳብ መግለጫዎችን እንደሚገመግሙ ተጠቅሷል። ይህንን መስፈርት ለማሟላት ተበዳሪዎች “ሀሰተኛ እና በትክክለኛ ኦዲተር ያልተሰራ” የሂሳብ መግለጫዎች ያቀርቡ እንደነበር፤ ብሔራዊ ባንክ ከቀረቡለት ሪፖርቶች መረዳቱን የመስሪያ ቤቱ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ይህ አካሄድ “በራሱ ወንጀል” መሆኑን ለባንኮች ባሰራጨው ደብዳቤ ላይ ያመለከተው ብሔራዊ ባንክ፤ ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች በሚያሳልፏቸው የብድር ውሳኔዎች ጥራት ላይ “አሉታዊ ተጽዕኖ” እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቁሟል። በዚህም ምክንያት ባንኮች “ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተሉ” እና በደንበኞች የሚቀርቡ የኦዲት ሪፖርቶች ላይ “ተገቢውን የማጣራት ስራ እንዲያከናውኑ” ብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ሀሰተኛ የሂሳብ ኦዲት መግለጫ የሚቀርብላቸው ባንኮችም “አስፈላጊውን የህግ እርምጃ” እንዲወስዱ በተጨማሪነት አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)