የተመድ የልማት ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሚውል 32.8 ሚሊዮን ዶላር ሊያሰባስብ ነው 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ሀገራዊ ምክክር ለመደገፍ 32.8 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ማቀዱ ተገለጸ። በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ከልማት አጋሮች ይሰበሰባል የተባለው ይኸው የድጋፍ ገንዘብ፤ UNDP በሚከፍተው “የፋይናንስ ቋት” አማካኝነት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ይተላለፋል ተብሏል። 

የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፉን ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ዛሬ ረቡዕ መስከረም 18፤ 2015 ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል። በገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት በተደረገው በዚሁ የስምምነት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት፤ የUNDP የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቱርሃን ሳለህ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የሚሰበሰበው ይህ ገንዘብ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሚመድበው ዓመታዊ በጀት ተጨማሪ እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሁለት ወር በፊት ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ፤ በበጀት ዓመቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚውል 208.6 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ የልማት አጋሮች ለማሰባሰብ ማቀዱን ገልጾ ነበር።

የምክክር ኮሚሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት ለሚያስፈጽማቸው ዕቅዶች የሚያስፈልገው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን 3.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነ በዚሁ ሰነዱ ላይ ጠቅሷል። ይህ የገንዘብ መጠን ከልማት አጋሮች ለማግኘት የታቀደውን ድጋፍ አይጨምርም። ለብሔራዊ ምክክሩ የገንዘብ ድጋፍ የሚያሰባስበው የተመድ የልማት ፕሮግራም፤ “እንደ አንድ የልማት አጋር” ለሂደቱ ማስፈጸሚያ የሚውል 2.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡ በዛሬው የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል።

UNDP ከሌሎች የልማት አጋሮች የሚያሰባስበው ገንዘብ የሚተዳደረው “ነጻ በሆነ የባለአደራ ፈንድ” (trust fund) እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው ጠቁሟል። የ“ትረስት ፈንዱ” መቋቋም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ  “በአዋጅ የተሰጡትን ኃላፊነቶች እንዲወጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል” ሲል የሚኒስቴሩ መግለጫ አትቷል። 

በታህሳስ 2014 በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “ሁሉን አቀፍ እና አካታች” ምክክር የማካሄድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “ተቋማዊ አቅሙን ለማጎልበት፣ ሁሉን አካታች እና አሳታፊ ሀገራዊ ምክክሮችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማስጀመር እንዲሁም በሀገሪቱ ወሳኝ የልዩነት ምክንያቶች ዙሪያ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ-ሐሳቦችን ለማመንጨት ለሚያደርገው ጥረት” በUNDP የሚቋቋመው የ“ትረስት ፈንድ” የራሱ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)