በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ መዓዛ መሐመድ እና አሳዬ ደርቤ ላይ ክስ መመስረቱን ዐቃቤ ህግ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ዐቃቤ ህግ፤ በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ መዓዛ መሐመድ እና በደራሲ አሳዬ ደርቤ ላይ “የሃሰት ወሬን በመንዛት፤ በውጊያ ውስጥ የወገን ጦር አሰላለፍና ቦታን ለጠላት እና ለህዝብ በመሳወቅ” ወንጀል ክስ መመስረቱን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።  በሶስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱ የተገለጸው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ አርብ ሊመለከተው የነበረው የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በዐቃቤ ህግ በቦታው አለመገኘት ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ ነው። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ዐቃቤ ህግ በሶስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ በአንድ መዝገብ አቀርበዋለሁ ያለውን ክስ ለመጠባበቅ ነበር። ሆኖም በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ዐቃቤ ህግም ሆነ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ሁለቱን ጋዜጠኞች ወክለው በችሎት የተገኙት ጠበቆች፤ ዐቃቤ ህግ በችሎት ባለመገኘቱ “መዝገቡን እንዳልፈለገው ተቆጥሮ” እንዲዘጋ ችሎቱን ጠይቀዋል። ከጠበቆቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ ጌታነህ፤ ገነት ሆቴል አቅራቢያ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በእስር ላይ ከምትገኘው መዓዛ መሐመድ ጋር ዛሬ ጠዋት በስልክ መነጋገራቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል። 

በወንጀል ምርመራ ቢሮ ለሚገኙ ፖሊሶች “ቀጠሮ እንዳለን ብንነግራቸውም ሊያቀርቡን ፈቃደኛ አይደሉም” ስትል መዓዛ እንደነገረቻቸው ጠበቃዋ ለችሎቱ አስረድተዋል። ሌላኛው ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው፤ የዛሬው ቀጠሮ በፍርድ ቤት የተሰጠው “ለመጨረሻ ጊዜ” ተብሎ መሆኑን አስታውሰዋል። ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው ዐቃቤ ህግ ባለበት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሄኖክ፤ ሆኖም ዐቃቤ ህግ ቀጠሮውን አክብሮ ባለመቅረቡ ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበት ጉዳይ ዋስትና የማያስከለክል ስለሆነ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ መዝገቡ እንዲዘጋላቸው ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል። 

የጠበቆችን መከራከሪያ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ መርማሪ ፖሊስ ሁለቱን ግለሰቦች ያላቀረበበትን ምክንያት በመጪው ሰኞ መስከረም 23 በችሎት ተገኝቶ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ አለመገኘት ላይ ምንም አይነት አስተያየት ሳይሰጥ ቀርቷል። 

ባለፈው ሰኞ መስከረም 16 በነበረው የችሎት ውሎ፤ ከሁለቱ ጋዜጠኞች ጋር በተመሳሳይ መዝገብ ክስ እንደሚቀርብበት በዐቃቤ ህግ ተነግሮለት የነበረው የደራሲ አሳዬ ደርቤ ጉዳይ ላይ ግን ችሎት የተለየ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ዐቃቤ ህግ በአሳዬ ላይ ክስ መመስረቱን አሊያም አለመመስረቱን ቀርቦ ባለመስረዳቱ ምክንያት፤ ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪው ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ተቀብሏል። በዚህ መሰረትም አሳዬ የአምስት ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈታ ውሳኔ አሳልፏል።

ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ካስተላለፈ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የፍትህ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ፤ ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ፣ ጎበዜ ሲሳይ እና አሳዬ ደርቤ ላይ ክስ መመስረቱን ይፋ አድርጓል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ክሱ የተመሰረተበትን ችሎት ባይገልጽም፤ ተጠርጣሪዎቹን ለክስ ያበቃቸውን ወንጀሎች ግን ዘርዝሯል።

በፍትህ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በአንደኛ ተከሳሽነት በተመዘገበው በጎበዜ ሲሳይ ላይ “ሶስት ተደራራቢ ክሶች” ቀርበዋል፡፡ በጋዜጠኛ ጎበዜ ላይ የቀረበው የመጀመሪያው ክስ፤ “በህዝብና እና በሰራዊት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ እሳቤ እንዲኖር” ሰርቷል፤ “የመንግስት የመከላከል አቅም ላይ ህዝቡ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ አስተላልፏል” የሚል ነው። 

ዐቃቤ ህግ ለዚህ ክስ ያቀረበው ማስረጃ፤ ጎበዜ ከአንድ ወር ገደማ በፊት “በትዊተር ስፔስ” አድርጎታል ያለውን ንግግር ነው። ጎበዜ በዚህ ንግግር “ጠቅላላ ህዝቡ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የማይደግፍ፤ ይልቁንም ህወሓት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የሚፈልግ እና የሚደግፍ እና ወጣቱ ከመንግስት ጎን መሰለፍ የማይፈልግ አድርጎ  አቅርቧል” ሲል ዐቃቤ ህግ ወንጅሏል። 

ጋዜጠኛው በግል የፌስቡክ ገጹ የጻፈው ጽሁፍ፤ በዐቃቤ ህግ ለቀረበበት ሁለተኛ ክስ ምክንያት ሆኗል። ጎበዜ ነሐሴ 30 በፌስቡክ ገጹ ባስነበበው ጽሁፍ “አሁን በተከፈተው ጦርነት ውስጥም ሕወሓትን ፊት ለፊት እየተዋጉ የሚገኙት የፋኖ መሪዎችን ምሬ ወዳጆን እና ደምሌ አራጋውን ለመግደል በተደጋጋሚ ከኋላ እየተተኮሰባቸው ህይዎታቸው ተርፏል። በዚህ ሁኔታ እንዴት መንግስትን ተማምኜ ጦርነት እገባለሁ የሚል ወጣትም አለ” ማለቱን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ ይህ መረጃ “ትክክል አለመሆኑን እያወቀ የሃሰት ወሬ የነዛ በመሆኑ” መከሰሱን ገልጿል። 

ሶስተኛው ጎበዜ ላይ የቀረበው ክስ “በውጊያ እንቅስቃሴ ውስጥ የወገን ጦር አሰላለፍ እና ቦታ፤ ለጠላት እና ለህዝቡ ማጋራት” የሚል ነው። ጋዜጠኛው ነሐሴ 30 በፌስቡክ ገጹ ባወጣው ጽሁፍ “የሃገር መከላከያ ሰራዊቱ እና ጥምር ጦሩ የት አካባቢ እንዳለ እና የት አካባቢ ሳይዝ እንደቀረ መግለጹን” የዐቃቤ ህግ የወንጀል ዝርዝር ያስረዳል። እነዚህ አይነት መረጃ “ከፍተኛ ቁምነገር ሆኖ መያዝ የሚገባው” መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ ይህን ተላልፎ መረጃውን በማጋራቱ ክስ እንደቀረበበት አትቷል። 

በሁለተኛ ተከሳሽነት የቀረበችውን ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ለክስ ያበቃት፤ በሶስተኛ ተከሳሽነት ስሙ ከተጠቀሰው አሳዬ ደርቤ ጋር በ “ሮሃ ሚዲያ” ላይ ያደረገችው ውይይት ነው። ሁለቱ ተከሳሾች በዚሁ ውይይታቸው “በወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም እና ስልቶች ምክንያት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ፍፁም ሐሰት በሆነ መንገድ በመቀየር፤ መንግስት ሆነ ብሎ ህወሃት ሲዳከም ጥቃት የሚያቆም እና እንዲጠናከር እድል የሚሰጥ፣ ለማሸነፍ ፍጹም ፍላጎት የሌለው አድርገው አቅርበዋል” በሚል ተወንጅለዋል። 

በዚህም መሰረት በጋዜጠኛ መዓዛ እና በደራሲ አሳዬ ላይ “የሐሰት ወሬዎችን በመንዛት” ክስ እንደቀረበባቸው በፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ላይ ተመልክቷል። ዐቃቤ ህግ በሶስቱ ተከሳሾች ላይ ዛሬ አርብ መስከረም 20፤ 2015 የመሰረተው ክስ በፍርድ ቤት ቀርቦ የመዝገብ ቁጥር መያዙን ፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል። ክሱ በመጪው ሰኞ መስከረም 23፤ 2015 ለተከሳሾች ደርሶ ክርክሩ እንደሚቀጥልም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)