የፌደራል መንግስት “ለማንኛውም ትንኮሳ አስፈላጊውን የማስታገሻ እርምጃ” እንደሚወስድ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አስጠነቀቁ

በሃሚድ አወል

የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ለሚደረገው ድርድር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚገፋበት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ። በመንግስት በኩል የቀረበውን “ይህን የሰላም አማራጭ በመርገጥ” ለሚደረግ “ማንኛውም ትንኮሳ” ግን “አስፈላጊው የማስታገሻ እርምጃዎች” እንደሚወሰዱ ፕሬዝዳንቷ አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ይህን ያሉት የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባን ዛሬ ሰኞ መስከረም 30፤ 2015 በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። ፕሬዝዳንቷ ያለፈውን ዓመት የመንግስት የስራ አፈጻጸም በዳሰሱበት እና የ2015 እቅድን በጠቆሙበት በዚሁ ንግግራቸው በመጀመሪያ ቅድሚያ ሰጥተው ያነሱት ጉዳይ፤ ከህወሓት ጋር ይደረጋል የተባለውን ውይይት ነው።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች “በጣም ተስፋ ሰጪ ውጤት” ማስመዘገቧን በንግግራቸው የጠቀሱት ሳህለወርቅ፤ ሆኖን “ግጭት እና መፈናቀል” አሁንም “ያልተሻገረቻቸው ችግሮች” መሆናቸው ገልጸዋል። “የሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ጦርነት እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሱ የጅምላ ጭፍጨፋዎች በአሉታዊ ጎናቸው የሚታወሱ ብቻ ሳይሆኑ የበርካቶቻችንን ልብ የሰበሩ ናቸው” ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ያለፈውን ዓመት ክስተቶች እና ውጤታቸውን በንግግራቸው አንስተዋል። 

በሀገሪቱ “ግጭት ጨርሶ እንዲያበቃ”፤ መንግስት ከማንኛውም ወገን ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር እና ልዩነቶችን በሰላም እና በወይይት ለመፍታት ሀሳብ ማቅረቡን ሳህለወርቅ አስታወሰዋል። ህወሓት “ለትግራይ ህዝብ ሲል” የሰላም ጥሪውን በመቀበል ለድርድር እንዲቀመጥ በተደጋጋሚ ጥሪ እንደቀረበለት ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል። “መንግስት ማንኛውንም አይነት ልዩነቶች በመነጋገር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ያምናል” ያሉት ሳህለ ወርቅ፤ “አሁንም ያለቅድመ ሁኔታ ለመወያየት ጥሪውን ያቀርባል” ብለዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“መንግስት የሰላም እና ዲሞክራሲ ጥያቄዎችን አንገብጋቢነት በመረዳት ቆራጥ ውሳኔ ባሳለፈው መሰረት፤ ከህወሓት ጋር የሀገሪቱን ጥቅም ባስከበረ እንዲሁም ዘለቄታን ባማከለ መልኩ ድርድር እንዲደረግ የተቻለውን ጥረት ይገፋበታል። ነገር ግን ይህን የሰላም አማራጭን በመርገጥ ለሚደረግ ማንኛውም ትንኮሳ አስፈላጊውን የማስታገሻ እርምጃዎች የሚወሰዱ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል” ሲሉም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አስጠንቅቀዋል። 

ርዕሰ ብሔሯ በዛሬው ንግግራቸው በአፍሪካ ህብረት በኩል ሲደረግ ነበር ያሉትን “የሰላም ጥረት” በበጎ አውስተውታል። “ህብረቱ በልዩ መልዕክተኛው በኩል እያደረገ ያለውን ጥረት በመቀጠል ለሰላም ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እምነቴ ነው” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)