በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንዱራ ወረዳ በደረሰ ጥቃት የወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ተገደሉ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን አንድ የክልሉ ባለስልጣን እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ትላንት ማክሰኞ ጥቅምት 1፤ 2015 በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉ ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት፤ ትላንትና ከሰዓት የተፈጸመው ጥቃት ኢላማ ያደረገው በመከላከያ ሰራዊት እና በፌደራል ፖሊስ አባላት ታጅበው በማንዱራ ወረዳ ከሚገኘው ቱኒ ቀበሌ ወደ ወረዳው ማዕከል በመጓዝ ላይ የነበሩ የወረዳው አመራሮችን ነው። በጥቃቱ የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሂስ ሄጮ እና ሹፌራቸው እንዲሁም አንድ የመከላከያ ሰራዊት እና ሶስት ፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪም በተመሳሳይ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። በጥቃቱ ቁጥራቸውን በወል ያላወቋቸው የጸጥታ ኃይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹት እኚሁ ነዋሪ፤ “ማታ ቁስለኞችን ሲያነሱ ነበር። ወደ ዘጠኝ አምቡላንስ አይቼያለሁ” ሲሉ የዓይን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከትላንቱ ጥቃት በኋላ ከመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ወደ ግልገል በለስ ከተማ የሚወስደው የተሽከርካሪ መንገድ ለትራፊክ ዝግ መደረጉን ነዋሪው አክለዋል። 

በማክሰኞው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ወደ ፓዌ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪ እና የክልሉ ኃላፊ ገልጸዋል። በፓዌ ጠቅላላ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ስለሚገኙ ቁስለኞች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ነመራ ኢቲቻ እና ለሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር አሰፋ ባየሩ ጥያቄ ብናቀርብም ሁለቱም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር  በትላንትናው ዕለት በማንዱራ ወረዳ ቱኒ ቀበሌ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም፤ በጥቃቱ ህይወታቸውን ስላጡ እና ጉዳት ስለደረሰባቸው ግለሰቦች ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ጥቃቱን የፈጸሙ ኃይሎች ማንነትን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ “ጫካ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እጅ ያልሰጡ አሉ። በእነሱ የደረሰ ጥቃት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኃላፊ በበኩላቸው “በአመራሮቹ ላይ ጥቃቱን ፈጸሙት የጉሙዝ ሽፍቶች እና አማጽያን ናቸው ” ሲሉ ይወነጅላሉ። የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪም “ድርጊቱን የፈጸሙት የአማጺው ጉሙዝ ሽፍቶች ናቸው” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙት መተከል እና ካማሺ ዞኖች ከዚህ ቀደም ለደረሱ ጥቃቶች፤ የክልሉ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ተጠያቂ የሚያደርጉት የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂዎችን ነው። ላለፉት ሁለት ዓመታት ታጣቂዎቹ ከክልሉ መንግስት ጋር በባህላዊ መንገድ እርቅ መፈጸማቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቢቆይም፤ በአካባቢዎቹ የሚፈጸሙት ጥቃቶች በየጊዜው መልሰው ሲያገረሹ ታይተዋል።  

የክልሉ መንግስት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር እርቅ ከፈጸመ በኋላ ጥቃት ሲደርስ የትላንትናው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ በክልሉ ካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። 

የትላንቱን ጥቃት በተመለከተ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ጥቃቱን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ እና የመተከል ዞን ሰላም ግንባታና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም ዋቅጅራ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)