ዶ/ር አለምነው መኮንን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

በሃሚድ አወል

የቀድሞው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶ/ር አለምነው መኮንን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። ዶ/ር አለምነው የኢንተርፕራይዝ ልማቱ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት፤ ተቋሙን ላለፉት 10 ወራት በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ብሩ ወልዴ ከኃላፊነታቸው በመልቀቃቸው ምክንያት ነው።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በአዲስ መልክ ከተዋቀሩ የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንዱ ነው። አዲሱ ተቋም በአዋጅ የፈረሰው የፌደራል አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ መብት እና ግዴታዎች ተላልፈውለታል። 

መስሪያ ቤቱ በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ከአራት ወራት በኋላ በዋና ዳይሬክተርነት የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት፤ የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን ከምስረታው ጀምሮ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲያስተዳድሩ የቆዩት አቶ ብሩ ወልዴ ነበሩ። አቶ ብሩ እስከ ትላንት ጥቅምት 2፤ 2015 በስራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩ የስራ ባልደረቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነታቸው “በገዛ ፍቃዳቸው” የለቀቁት ከዛሬ ጥቅምት 3፤ 2015 ጀምሮ መሆኑን አቶ ብሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ብሩ ለዚህ ውሳኔ የበቁት “በግል ምክንያት” መሆኑን ከመግለጽ ባሻገር በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

የዋና ዳይሬክተሩን ከኃላፊነት መልቀቅ የኢንተርፕራይዝ ልማት መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ አረጋግጠዋል። በተሰናባቹ ኃላፊ ምትክ ዶ/ር አለምነው መኮንን መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተቋሙ መድረሱንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተፈረመ ደብዳቤ መሾማቸው የተገለጸው ዶ/ር አለምነው፤ የቀድሞው ብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ። የብአዴን እና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ዶ/ር አለምነው፤ በኢህአዴግ የመጨረሻ ዓመታት ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ የአማራ ክልል አመራሮች አንዱ ነበሩ።

ዶ/ር አለምነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሚኒስትር ማዕረግ የቀድሞው የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ሆነው በሚያዚያ 2010 ዓ.ም ተሾመው ነበር። በአሁኑ ወቅት “የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ” የሚል ስያሜ በያዘው በመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በኃላፊነት የቆዩት ግን ለሰባት ወራት ያህል ብቻ ነበር።

የቀድሞው ገዢ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ቀጣይ መዳረሻቸው የሆነው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካኝነት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በህዳር 2011 ዓ.ም የተሾሙት  አለምነው፤ በዚሁ የኃላፊነት ቦታቸው ላይ እያሉ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመስራት ወደ ቻይናው ፔኪንግ ዩኒቨርሲቲ አቅንተዋል። ባለፈው ግንቦት ወርም ከዩኒቨርስቲው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ“theoretical economics” አግኝተዋል።

አዲስ ዋና ዳይሬክተር ያገኘው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። ይህ የመንግስት ተቋም የሚኖሩትን ስልጣን እና ተግባራት በተመለከተ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚወጣ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ቢገልጽም፤ እስካሁን ተግብራዊ አልሆነም። ተቋሙን የሚመለከተው ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን እና በቅርቡ ይጸድቃል ብለው እንደሚጠብቁ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)