ውስኪ እና የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎችን ጨምሮ ለበርካታ ሸቀጦች የውጭ ምንዛሬ ተከለከለ  

ውስኪ፣ የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎች እና የተለያዩ የሥጋ አይነቶችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ለምትሸምታቸው በርካታ ምርቶች እና ሸቀጦች “ላልተወሰነ ጊዜ” የውጭ ምንዛሬ እንደማይፈቀድ የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ  አርብ  ጥቅምት 4፤ 2015 አስታውቋል። በውሳኔው የውጭ ምንዛሬ ከተከለከሉ ምርቶች መካከል የሰው እና አርቴፊሻል ጸጉሮች፣ የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢሎች ፣ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎች ይገኙባቸዋል። 

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋስው ለብሔራዊ ባንክ በጻፉት ደብዳቤ፤ ውሳኔው የተላለፈው የማክሮ ኮሚቴ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። ውሳኔው “የዋጋ ንረት በህብረተሰቡ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ሲባል የተወሰዱ እርምጃዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ” ሲባል የተላለፈ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ምንዛሪ አመዳደብ ረገድ “ለመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች፣ ለመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች” ትኩረት እንደሚሰጥ በደብዳቤው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ “ከውጭ ገብተው በአገር ውስጥ እሴት ተጨምሮባቸው ገቢ ምርቶችን ለመተካት የሚውሉ ምርቶች ለማምረት የሚውሉ ግብዓቶች የካፒታል ዕቃዎች” በአዲሱ ውሳኔ ተመሳሳይ ትኩረት አግኝተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)