የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ሌብነት” እና “ብልሹ አሰራርን” መታገል “ፈተና ሆነውብኛል” አለ 

በሃሚድ አወል


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሌብነትን እና ብልሹ አሰራር ውስጥ የገባውን የአገልግሎት አሰጣጥ መታገል “ፈተና እንደሆኑበት” የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አበቤ ገለጹ። ከመሬት ዘረፋ እና ህገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ የህግ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ረገድ፤ በፍትህ አካላት በኩል “በቂ ትኩረት አላገኘም” ሲሉ ከንቲባዋ ተችተዋል። 

ከንቲባ አዳነች ይህን የገለጹት የሚመሩትን የከተማ አስተዳደር የ2015 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባቀረቡበት ባለ 16 ገጽ ሪፖርት ነው። ለከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ዛሬ አርብ ጥቅምት 4፤ 2015 በንባብ የቀረበው ይህ ሪፖርት ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው፤ በሰላም እና ጸጥታ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በኑሮ ውድነት እንዲሁም በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ነው። 

ከንቲባዋ በዚሁ ሪፖርታቸው “በ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያሳካናቸው ትልልቅ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ሌብነት እና ብልሹ አሰራር ውስጥ የመግባት ችግር እና አገልግሎትና ጽንፈኝነትን መታገል ፈተና ሆነው ጎልተው ወጥተዋል” ሲሉ ለአስተዳደሩ ፈተና ሆነዋል ያሏቸውን ጉዳዮች አጽንኦት ሰጥተዋል። ፖለቲካዊ ተጠያቂነት ማስፈን ላይ “የተሻለ ጥረት መኖሩን” በሪፖርታቸው ያወሱት አዳነች፤ የህግ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ላይ ግን ድክመት እንደሚታይ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ለብልሹ አሰራር መነሻ የሆኑ” ያላቸውን አመራሮች እና ባለሙያዎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ከፍትህ አካላት የሚያገኘው ትብብር “በቂ” እንዳልሆነም ከንቲባዋ አመልክተዋል። “በመሬት ወረራ እና ህገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ በቂ ማስረጃም አቅርበን እያለ፤ በፍትህ አካላት በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ የምክር ቤቱ ድጋፍና ትኩረት ያሻዋል” ሲሉ በዛሬው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለተገኙ አባላት አሳስበዋል። 

ከመሬት ወረራ፣ ህገ ወጥ ግንባታ እና ብልሹ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ በሚገኙ ሶስት ተቋማት እና አምስት ክፍለ ከተሞች የነበሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አዳነች አስረድተዋል። ከንቲባዋ የተቋማቱን እና የክፍለ ከተሞችን ማንነት በሪፖርታቸው ቢያካትቱም፤ የአመራሮቹን እና ባለሙያዎቹን ዝርዝር መረጃ ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።  

“ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ” እንደተወሰደባቸው የተገለጹት የተቋማት አመራሮች እና ባለሙያዎች፤ በከተማይቱ ትራንስፖርት ቢሮ፣ በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዲሁም በዲዛይን እና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው። ተመሳሳይ እርምጃ የተወሰደባቸው የከተማይቱ ክፍለ ከተሞች ለሚ ኩራ፣ ቂርቆስ፣ ልደታ፣ የካ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ መሆናቸው በከንቲባይቱ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ፈተና ሆነውበኛል” ካላቸው ጉዳዮች በተጨማሪ፤ ባለፈው ሩብ ዓመት “ተጠቃሽ ችግሮች” ያላቸው ተግዳሮቶች በዛሬው የከንቲባ አዳነች ሪፖርት ላይ ተዘርዝረዋል። በሃይማኖት እና በብሔር መልክ የሚገለጽ ጽንፈኝነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እጥረት እንዲሁም የኑሮ ውድነት እና የገበያ ዋጋ መናር በሪፖርቱ በችግርነት የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። 

ከንቲባ አዳነች በከተማይቱ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ አመራራቸው የወሰዳቸውን እርምጃዎች ለምክር ቤት አባላቱ አብራርተዋል። “የምርት አቅርቦት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል” ያሉት አዳነች “በአቅርቦት ችግር ምክንያት” ለሸማቾች ለማቅረብ ከታቀደው 360 ሺህ ኩንታል ስኳር ማሰራጨት የተቻለው ከግማሽ በታች መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው የከተማ አስተዳደሩ በዕቅዱ ልክ ማሳካት ያልቻለው የስራ ዕድል ፈጠራን ነው። የከተማ አስተዳደሩ ለ60 ሺህ ስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ማሳካት የቻለው ግን ለ36 ሺህ ሰዎች ብቻ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ይህም ከዕቅዱ 60 በመቶ ያህሉን የሚሸፍን ነው። 

“የስራ ዕድል [ፈጠራ] አንዱ የትኩረት ማዕከላችን ነው። ብዙ ርብርብ እያደረግንም ነው” ያሉት ከንቲባዋ፤ “ነገር ግን እናንተም እንዳያችሁት ብዙ ጠብ አይልም” ሲሉ ጉዳዩ በታቀደው ልክ አለመሳካቱን ጠቁመዋል። አዳነች አቤቤ “ከስራ ዕድል [ፈጠራ] አንጻር ትልቁ ተግዳሮት ፍልሰት ነው” ሲሉ ለዕቅዱ አለመሳካት ምክንያት ነው ያሉትን ጉዳይ አንስተዋል። 

ከንቲባዋ አክለውም “በፖለቲካዊ እና ሌሎች ማህበራዊ ፍላጎቶችም ወደ ከተማይቱ ጤነኛ ያልሆነ ፍልሰት ይታያል” ብለዋል። አዳነች በሩብ ዓመቱ “በህገ ወጥ መንገድ ለማይገባቸው ግለሰቦች ተሰጠ” ካሉት 4,649 ቀበሌ መታወቂያ 99 በመቶውን ያገኙት “የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል። 

አዳነች “ጤነኛ ያልሆነ” ያሉት “ፍልሰት”፤ “ለውጥ ሊያመጣ የማይችል በመሆኑ በፖሊሲ እና በቅንጅት ስነ ስርዓት መያዝ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም ከክልሎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አክለዋል። 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሩብ ዓመቱ “በህገ ወጥ መንገድ ለማይገባቸው ግለሰቦች ተሰጠ” ካሉት 4,649 ቀበሌ መታወቂያ 99 በመቶውን ያገኙት “የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሩብ ዓመቱ በዋናነት “ውጤት ያመጣበት” የተባለው ስራ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር የተያያዘ ነው። አዳነች “ከተማችንን ከፍተኛ ትምርስ እና ሁከት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል የነበረ የጥፋት ኃይሎችንና ህገ ወጥ መሳሪያንም መቆጣጠር ተችሏል” ብለዋል። ከንቲባዋ ከዚህ በተጨማሪም በከተማይቱ “የጥፋት ኃይሎች ለመፈጸም አቅደዋቸው የነበሩ የጥፋት ሴራዎችን ለማክሸፍ” 1.5 ሚሊዮን የአዲስ አባባ ነዋሪዎች መደራጀታቸውን በስኬትነት ጠቅሰዋል።  

ሌላው በስኬት የተነሳው ጉዳይ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን መካከል የተደረገው የአስተዳደር ወሰን ማካለል ነው። ከንቲባዋ በሪፖርታቸው የወሰን ማካለል በመደረጉ “ተቀብሮ የነበረው ተንኮልና የግጭት መቀስቀሻ አጀንዳ በጥበብ፣ በብስለትና ኃላፊነት በተሞላበት አመራር ማምከን ተችሏል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)