በሃሚድ አወል
የታሸገ ውሃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በምርቶቻቸው የመሸጫ ዋጋ ላይ ከሁለት ወራት በኋላ መጠነኛ ቅናሽ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር አስታወቀ። የዋጋ ማስተካከያው የሚደረገው፤ ፋብሪካዎቹ ውሃውን ለሚያሽጉበት የፕላስቲክ ጠርሙስ የሚውል “ማስተርባች” የተሰኘ ጥሬ ዕቃ መጠቀም እንዲያቆሙ መወሰኑን ተከትሎ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፤ የውሃ መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙስን ሰማያዊ ቀለም እንዲይዝ የሚያደርገውን ይህን ጥሬ ዕቃ በአገልግሎት ላይ እንዳይውል ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነው። ከሶስት ወራት በፊት በተላለፈው ውሳኔ መሰረት፤ የታሸገ ውሃ አምራች ፋብሪካዎች ካለፈው ሳምንት አንስቶ ምርቱን መጠቀም ማቆም መጀመራቸውን የኢትዮጵያ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ መርዕድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የታሸገ ውሃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች “ማስተርባች” የተሰኘውን ጥሬ ዕቃ ከውጭ ለማስገባት በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያወጡ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ “እነዚህ አምራቾች ይህንን ምርት ማስገባት ሲያቆሙ በተወሰነ ደረጃ ወጪ እንደሚቀንሱ ይጠበቃል” ብለዋል። የታሸገ ውሃ የመሸጫ ዋጋ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ ሁለት ወራት መጠበቅ ያስፈለገውም፤ አምራቾቹ “ማስተርባች” የተሰኘውን ጥሬ ዕቃ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እስከሚያቆሙ ድረስ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰማንያ ዘጠኝ የታሸገ ውሃ አምራች ፋብሪካዎችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር፤ የዋጋ ማስተካከያውን በተመለከተ ከአባላቱ ጋር መነጋገሩንም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል። “ለማስተርባች የሚወጣው ወጪ ይታወቃል። ሁሉም ውሃ አምራቾች ከዚህ በኋላ ለዚያ የሚያወጡት ወጪ አይኖርም። ስለዚህ የተወሰነ ያህል [ዋጋቸውን] መቀነስ እንዳለባቸው ይጠበቃል” የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ “ነጻ ገበያ ስለሆነ ዋጋ መተመን አንችልም፤ ነገር ግን አማካኝ ዋጋ ይወጣለታል” ሲሉ የዋጋ ማስተካከያው ስለሚደረግበት ሂደት አብራርተዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ መሰረት በአሁኑ ወቅት የታሸገ ግማሽ ሊትር ውሃ ከ12 እስከ 15 ብር ሲሸጥ፤ አንድ ሊትር ደግሞ ከ17 እስከ 20 ብር ይሸጣል። የውሃ አምራች ፋብሪካዎች፤ ባለ ግማሽ ሊትር ደርዘን የታሸገ ውሃ ለሱቆች የሚያስረክቡት በ110 ብር ዋጋ ነው። ባለ ሱቆች ስድስት ፍሬዎች የያዘ፣ ባለ ሁለት ሊትር የታሸገ ውሃ በጅምላ ከፋብሪካዎች የሚረከቡትም በተመሳሳይ በ110 ብር ዋጋ ነው።
የኢትዮጵያ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር በእነዚህ የመሸጫ ዋጋዎች ላይ ማስተካከያ የሚደረግበትን ምክረ ሀሳብ ይዞ ከመምጣቱ በፊት፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር “ማስተርባች” የተሰኘውን ጥሬ ዕቃ በተመለከተ ለአንድ ዓመት ያህል ጥናት ማድረጉን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል። በዚህ ጥናት ላይ ማህበሩ ተሳትፎ እንደነበረው የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ በጥናቱ መሰረት “የፕላስቲኩን ቀለም ሰማያዊ ማድረግ አስገዳጅ” አለመሆኑ ከስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

“በጥናቱ መሰረት ከጤና ተጽዕኖ፣ ከውጭ ምንዛሬ እና ከአካባቢ ጥበቃ አንጸር ምርቱን መጠቀም መቅረት እንዳለበት ተወስኗል” ሲሉ የጥናቱን ግኝት አስረድተዋል። ውሃ የሚታሸግባቸው ፕላስቲኮች “ማስተርባች” የተሰኘውን ጥሬ ዕቃ “አካባቢ ላይ ሲጣሉ በቀላሉ አይበሰብሱም” ሲሉም ለውሳኔው መተላለፍ ምክንያቶች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የአካባቢ ብከላ ጉዳይ በምሳሌነት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር በአባልነት ያቀፋቸው አምራቾች፤ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን መቆጣጠር እንደሚጀምር አቶ አሸናፊ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ካሉ 107 የታሸገ ውሃ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ፤ የማህበሩ አባል ያልሆኑ አምራቾች አስራ ስምንት ብቻ ናቸው። ከአምስት ዓመታት በፊት በ2010 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የተመሰረተው ይህ ማህበር፤ ከታሸገ ውሃ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተጨማሪ የለስላሳ መጠጦች፣ ጁስ እና የፕላስቲክ ውጤቶች የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችንም በአባልነት ያቀፈ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)