የበረታ ውጊያ የሚደረግበት የሰሜን ኢትዮጵያ ሁኔታ “ከቁጥጥር ውጪ” እየሆነ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናገሩ። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በበኩላቸው እየተደረገ ነው የተባለው “ኃይለኛ ውጊያ”፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተደጋጋሚ የገለጹትን “ቁርጠኝነት የሚቃረን ነው” ሲሉ ተችተዋል።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያን በተመለከተ ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን የሰነዘሩት፤ ትላንት ሰኞ ጥቅምት 7፤ 2015 በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ አጠገብ ለተገኙ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው። የተመድ ዋና ጸሀፊ በዚሁ መግለጫቸው “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው። ኹከት እና ውድመት ከአሳሳቢ ደረጃ ደርሷል። ማህበራዊ መስተጋብር እየተበጣጠሰ ነው” ብለዋል።
በትግራይ ክልል “በመኖሪያ አካባቢዎች ጭምር በጅምላ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በየቀኑ በርካታ ንጹሐን ሰዎችን እየገደሉ፣ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እያወደሙ እና አንገብጋቢ አገልግሎቶች የማግኘት ዕድል እየገደቡ ነው” ሲሉም የሁኔታውን አሳሳቢነት ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። “በሴቶች፣ ሕፃናት እና ወንዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እና ሌሎች ጭካኔዎች መፈጸማቸውን የሚገልጹ ረባሽ ምስክርነቶች እየሰማን ነው” ሲሉም የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አክለዋል።
ለአምስት ወራት በተኩስ አቁም ጋብ ብሎ የነበረው ውጊያ ባለፈው ነሐሴ ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ “በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች” ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉ የተናገሩት ጉተሬዝ፤ አብዛኞቹ ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደገጠማቸው ገልጸዋል። በትግራይ ያለው ግጭት ሊቆም እንደሚገባ የወተወቱት የተመድ ዋና ጸሀፊ፤ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተነጥሎ ከኢትዮጵያ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኤርትራ ጦር ጉዳይ፤ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ መንግስት በትላትናው ዕለት ባወጧቸው መግለጫዎች ላይም በተደጋጋሚ ተነስቷል። ትላንት ሰኞ በሉግዘምበርግ በአንገብጋቢ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የተገናኙት የአውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባቸውን ሲያጠናቅቁ፤ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከኤርትራ መከላከያ ኃይል ጋር በጥምረት እያካሄደ ነው” ያሉት “ወታደራዊ ጥቃት” እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ፤ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ጠቅልሎ እንዲወጣ በመጠየቅ ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ህብረት የያዘውን አቋም በድጋሚ አጠናክረዋል። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች “ግጭቱን ከማቀጣጠል ይልቅ በማርገብ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም” ጥሪ አቅርበዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በመግለጫቸው የኢትዮጵያን ጎረቤቶች ቢጠቅሱም የሀገራቱን ስም ግን በስም ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ውጊያ መስፋፋት፤ ከሚያስከትላቸው ከፍተኛ ውድመት፣ መፈናቀል፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች የከፉ ከማድረግ ባሻገር፤ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ቃል አቀባይ ቬዳንት ፓቴል ትላንት ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ውጊያው በተመለከተ ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል።
ቃል አቀባዩ በሰሜን ኢትዮጵያ “የግጭት መጨመር፣ ሞት፣ ሰላማዊ ሰዎች ያለ ልዩነት ኢላማ መሆን እና ውድመት መቀጠሉ ያሳስበናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ፓቴል በዚሁ መግለጫቸው፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኤርትራ ጦር በጥምረት የጀመሩትን ወታደራዊ ጥቃት እንዲያቆሙ ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ አስተጋብተዋል።
ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት መነጋገራቸውን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። በተሾሙ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ የመጡት ማይክ ሐመር፤ ውጊያውን ለማቆም እና ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላም ንግግር እንዲያመሩ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ሐመር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በባህርዳር በተደረገው የ“ጣና ፎረም” ጉባኤ ላይ በተገኙበት ወቅትም፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ውጊያ በውይይት ለመፍታት ጊዜው አሁን እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ነበር። ልዩ ልዑኩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሊደረግ ለታሰበው የሰላም ድርድር አሜሪካ ያላትን ድጋፍ በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ቃል አቀባይ በትላንቱ መግለጫቸው ሀገራቸው የአፍሪካ ህብረት ያቀረበውን ጥሪ እንደምትደግፍ አሳውቀዋል። ምክትል ቃል አቃባዩ የጠቀሱት የአፍሪካ ህብረት ጥሪ “በአስቸኳይ ያለ ቅድመ ሁኔታ ተኩስ እንዲቆም እና ሰብዓዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀመሩ” ያሳሰበ ነው። የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ይህን ጥሪ ያቀረቡት ከትላንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 6፤ 2015 ነበር።
የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የሚመሩት ድርጅት “የኢትዮጵያ ሕዝብ የገጠመውን አስፈሪ ቅዠት ለማብቃት የአፍሪካ ህብረትን በሁሉም መንገድ ለማገዝ ዝግጁ” መሆናቸውን በትላንቱ መግለጫቸው አስታውቀዋል። ሆኖም ጉተሬዝ የሰላም ንግግሩ በአፋጣኝ ሊጀመር ይገባል የሚል አቋም አላቸው። “ወደ ውጤታማ እና ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ የሚያመራ ንግግር በአፋጣኝ እንዲጀመር እንሻለን” ያሉት የተመድ ዋና ጸሐፊ “ወታደራዊ መፍትሔ የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት እና የኢትዮጵያን መረጋጋት፣ የግዛት አንድነት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚችለው በሰላም ንግግር ብቻ እንደሆነ አቋማቸውን የገለጹት የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል። አዲ ዳዕሮ በተባለ ቦታ እና በሽሬ ከተማ በቅርቡ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ጨምሮ እየተደረገ ነው የተባለው “ኃይለኛ ውጊያ”፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተደጋጋሚ የገለጹትን “ቁርጠኝነት የሚቃረን” እንደሆነም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ተችተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው የመከላከል እርምጃ የኢትዮጵያን “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር” ያለመ እንደሆነ ገልጿል። የፌደራል መንግስት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ “የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የፌደራል ተቋማትን እና ታላላቅ መሰረተ ልማቶችን” እንደሚጠበቅም አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን መግለጫ ከማውጣቱ አንድ ቀን አስቀድሞ ህወሓት “በአስቸኳይ የግጭት ማቆም ስምምነት ለመገዛት” ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)