የመከላከያ ሰራዊት የሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን መቆጣጠሩን የኢትዮጵያ መንግስት አረጋገጠ

በትግራይ ክልል የሚገኙትን የሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን የመከላከያ ሰራዊት መቆጣጠሩን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ። የአማራ እና የትግራይ ክልሎችን በሰሜን ጎንደር እና በወልዲያ በኩል የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎችን ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑም የፌደራል መንግስት አስታውቋል።

በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የምትገኘው ሽሬን ጨምሮ የአላማጣ እና የኮረም ከተሞች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መግባታቸው የተገለጸው፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ነው።  የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ መግለጫ፤ የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው “ከፍተኛ ጥንቃቄ” እስካሁን ድረስ በሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ላይ ጉዳት አለመድረሱን ጠቅሷል። 

የመከላከያ ሰራዊት ያሳየው ከፍተኛ ጥንቃቄ “አንዳንዶች የህወሓትን ፕሮፖጋንዳ በማስተጋባት የተነበዩትን አሳዛኝ ሁኔታ ማስቀረት ችሏል” ሲልም ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” ሲሉ አስታውቀው ነበር። 

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “አንዳንዶች ሊስሉት ከፈለጉት በተቃራኒ ግጭቱ ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ አይደለም” ብለዋል። አቶ ሬድዋን ግጭቱ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ የነበረው ወደ ሌሎች ክልሎች በተስፋፋበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ግን ይህ “እየጠፋ እና እየከሰመ” ይገኛል ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው መግለጫው ያነሳው ሌላው ጉዳይ፤ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና መሰረታዊ አገልግሎቶች ማስቀጠልን የተመለከተ ነው። የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በኩል ከሚመለከታቸው የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ አስታውቋል። 

በመግለጫው መሠረት ይህ ጥረት ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚጓጓዝባቸውን መስመሮች ማስፋትን የሚጨምር ነው። በዚህም መሠረት በሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሽሬ የሚያመራውን እና በኮምቦልቻ ደሴ፣ ወልድያ፣ ቆቦ እና አላማጣ በኩል የሚያልፈውን መስመር ለመክፈት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ የዕርዳታ ስርጭት ስራው በትግራይ ከሰባት ሳምንታት በላይ መቋረጡን፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎችም መስተጓጎሉን የተመድ ዋና ጸሀፊ ትላንት ሰኞ ተናግረው ነበር። 

በሶስቱ ክልሎች ዳግም ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት 13 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እና ሌሎች እርዳታዎች ፈላጊ እንደነበሩ ዋና ጸሀፊው በትላንቱ መግለጫቸው አስታውሰዋል። ጉተሬዝ ሁሉም ወገኖች እርዳታ ለሚሹ ሰላማዊ ሰዎች ሰብዓዊ እገዛ ያለ ገደብ የሚደርስበትን መንገድ በአፋጣኝ እንዲያመቻቹ በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)