ኢትዮጵያ መንግስት የልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው የሰላም ንግግር ወደ ስፍራው መጓዙ ተገለጸ  

በሃሚድ አወል

ከህወሓት ጋር ለሚደረገው የሰላም ንግግር ኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸውን የፌደራል መንግስት አስታወቀ። መንግስት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች “ከየአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመነጋገር ህዝባዊ አስተዳደር የሚቋቋምበትን መንገድ” እያመቻቸ እንደሚገኝ አስታውቋል።

መንግስት ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 14፤ 2015 በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በኩል ባወጣው መግለጫ ነው።  አገልግሎቱ በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት የደቡብ አፍሪካውን የሰላም ንግግር “ግጭቱን በሰላም ለመፍታት የሚቻልበት ዕድል አድርጎ ይመለከተዋል” ብሏል። 

የህወሓት ቃል አቀባይ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በተመሳሳይ በሰላም ንግግሩ ላይ ለመሳተፍ የህወሓት ልዑካን ቡድን ደቡብ አፍሪካ መግባቱን ትላንት ምሽት በትዊተር ገጻቸው አስታውቀው ነበር። የፌደራል መንግስትም ሆነ ህወሓት በሰላም ንግግሩ የሚሳተፉ የልዑካን ቡድን ውስጥ  ስለተካተቱ ግለሰቦች ያሉት ነገር የለም። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ “የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ” ማቋቋማቸው ይታወሳል። ኮሚቴው ከህወሓት ጋር በሚደረገው ውይይት የፌደራል መንግስቱን የሚወክል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተናግረው ነበር። 

ሰባት አባላት ባሉት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዮስ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተካትተዋል። የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት ከፌደራል መንግስት ጋር ለሚደረገው ድርድር፤ የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የሚገኙበት ቡድንን መወከሉን ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)