ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሌብነት እና ምርት ሥወራ” የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኞቹ ፈተናዎች መሆናቸውን ገለጹ። ፈተናዎችን የሚሻገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከተፈለገ እነዚህን ተግዳሮቶች “ማጥፋት” እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህን ያሉት ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 14፤ 2015 ከብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን ጋር ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። የዛሬው ስብሰባ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ያለበት ደረጃ የገመገመ ነው ተብሎለታል።
“በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንኳን ችግር ተቋቋሚ ኢኮኖሚ ሊኖረን ችሏል” ሲሉ በመልዕክታቸው ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ “ዋነኛ ፈተናዎች” ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል። “የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሌብነት እና ምርት ሥወራ ዋነኞቹ ፈተናዎቻችን ሆነዋል” ያሉት አብይ፤ እነዚህን ለማጥፋት “የሁላችንም ወሳኝ ትግል ይፈልጋል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው “የብልጽግና እንቅፋቶች” ተግባራትም ጠቅሰዋል። “ወደ ውጭ መላክ የሚገባውን ምርት መደበቅ፣ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር እና መሬትን በአሻጥር መውረር” የብልጽግና ዕንፋቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ “በቆራጥነት ፈጣን እርምጃ” ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፈተናዎችን የሚሻገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ይቻል ዘንድ “ገቢን የመጨመር እና ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ የልማት ትግል ይጠበቅብናል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል። የኢኮኖሚ ዋነኛ ፈተናዎችን የተባሉትን “ማጥፋት” ከተቻለ እና “ገቢ ማሳደግ እና ወጪ መቀነስ” ተግባራዊ ከተደረገ፤ “በራስ ፖሊሲ እና በራስ አቅም ማደግ” እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)