በጦርነት ምክንያት ተዘግቶ የቆየው የወልድያ – አላማጣ መንገድ ለተሽከርካሪዎች ክፍት ተደረገ 

በሃሚድ አወል

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ዝግ ሆኖ የነበረው ከወልድያ፣ ቆቦ፣ አላማጣ የሚወስደው መንገድ ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት እና ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከወልድያ እስከ ቆቦ ባለው አውራ ጎዳና ለህዝብ ትራንስፖርት ክፍት የሆነው ከባለፈው ሳምንት አጋማሽ ሲሆን፤ ከቆቦ እስከ ዋጃ ከተማ ባለው መንገድ የመጓጓዣ አገልግሎት የተጀመረው ደግሞ ትላንት ሰኞ መሆኑን ባለስልጣናቱ እና ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል። 

ከወልድያ እስከ አላማጣ ባለው መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት መሰጠት የተጀመረው፤ የአማራ እና የትግራይ ክልሎችን በሁለት መስመሮች በኩል የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎችን ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፌደራል መንግስት ባለፈው ሳምንት ካስታወቀ በኋላ ነው። የመጀመሪያው መስመር በሰሜን ጎንደር አቅጣጫ በኩል ያለ ሲሆን በአዲ አርቃይ፣ ማይጸምሪ አድርጎ ወደ ሽሬ ከተማ የሚያመራ ነው። 

በኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልድያ፣ ቆቦ እና አላማጣ በኩል የሚያልፈው ሁለተኛው መስመር ደግሞ የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞንን ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጋር የሚያገናኝ ነው። ይህ መንገድ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ተዘግቶ ከቆየ በኋላ ባለፈው ዓመት አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ነበር። ሆኖም በአካባቢው ባለፈው ነሐሴ ወር ዳግም ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ለመዘጋት ተገድዷል።

ላለፉት ሁለት ወራት ለህዝብ ማጓጓዣ ዝግ ሆኖ የቆየው ከወልድያ ቆቦ የሚወስደው መንገድ፤ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ለትራንስፖርት ክፍት መደረጉን የወልድያ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ዳዊት መለሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህንን የከንቲባውን ገለጻ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የከተማይቱ ነዋሪም አረጋግጧል። 

በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በዋናነት እየሰጡ የሚገኙት የ“ሚኒባስ” ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ይኸው ነዋሪ ገልጿል። ከወልድያ ወደ ቆቦ “ሹፌሮች ታሪፍ እያስወደዱ ነው እንጂ ሰዎች በአባዱላ እየተጓጓዙ ነው” የሚለው ነዋሪው፤ ከቆቦ ወደ ወልድያ በሚደረገው ጉዞ ግን አሽከርካሪዎች ተሳፋሪ ስለማያገኙ “ብዙ ጊዜ ባዷቸውን” እንደሚመለሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል። 

በወልድያ እና ቆቦ ከተሞች መካከል ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በዋናነት እየሰጡ የሚገኙት የ“ሚኒባስ” ተሽከርካሪዎች ናቸው | ፎቶ፦ ቴዎድሮስ አያሌው

ከወልድያ ወደ ቆቦም ሆነ፤ ከቆቦ ወደ ዋጃ በሚደረገው ጉዞ የሚጠየቀው ዋጋ ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ የጨመረ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከወልድያ ቆቦ ከዚህ በፊት ለአንድ ጉዞ የሚጠየቀው ታሪፍ 50 ብር እንደነበር የሚጠቅሱት የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎች፤ አሁን ዋጋው ወደ መቶ ብር ማሻቀቡን ገልጸዋል። 

ከቆቦ በ16 ኪሎሜትር ርቅት ወደምትገኘው ዋጃ ለመሄድ ከዚህ ቀደም ይከፈል የነበረው ከ10 እስከ 15 ብር እንደነበር የምታስታውሰው አንድ የቆቦ ነዋሪ፤ በትላንትናው ዕለት ተሳፋሪዎች 50 ብር እንዲከፍሉ ሲጠየቁ ተመልክቼያለሁ ብላለች። በትራንስፖርት ታሪፉ ላይ ጭማሪ መስተዋሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የቆቦ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰጠ ዋሴ፤ ምክንያቱ “የነዳጅ ችግር ስላለ እና አገልግሎቱ ተቋርጦ ስለከረመ ነው” ይላሉ። 

“በቀጣይ ትክክለኛ እና መደበኛ ታሪፍ ወጥቶለት ህዝቡም ሳይጎዳ አገልግሎት ይሰጣል” ሲሉም ወደፊት በታሪፉ ላይ ማስተካከያ እንደሚደረግ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ጠቁመዋል። ከዋጃ እስከ አላማጣ ያለው መንገድ ለህዝብ ትራንስፖርት ክፍት የሚሆንበትን ቀን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሰጠ፤ “እሱ ነገር ገና ነው። [ሆኖም] ከዚህ በኋላ ብዙም የሚከብድ ነገር አይደለም። መቼ እንደሚሆን እርግጠኛ አይደለንም እንጂ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ይጀመራል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)