የተመድ፣ የአሜሪካ መንግስት እና የኢጋድ ተወካዮች በሰላም ንግግሩ በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው – ሙሳ ፋኪ ማህማት

ዛሬ በደቡብ አፍሪካ በተጀመረው የሰላም ንግግር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ የአሜሪካ መንግስት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ተወካዮች “በታዛቢነት” እየተሳተፉ እንደሚገኙ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት አስታወቁ። ሊቀመንበሩ ይህን ያስታወቁት በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የሰላም ንግግር መጀመሩን አስመልክቶ ዛሬ ማምሻውን ባወጡት መግለጫ ነው።

ማህማት በዚሁ መግለጫቸው፤ የዛሬ የሰላም ንግግር ሁለቱ ወገኖች “ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙበት” እንደሆነ ገልጸዋል። ከተቀሰቀሰ ሁለት ዓመት ሊደፍን አንድ ሳምንት ገደማ ለቀረው የትግራይ ጦርነት “ፖለቲካዊ መፍትሔ” ለማበጀት፤ የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለረጅም ጊዜ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዛሬ በደቡብ አፍሪካ በይፋ የተጀመረው የሰላም ንግግር የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ህብረት በሚያቀነቅነው “ለአፍሪካ ችግሮች፤ አፍሪካዊ መፍትሔ” የማፈላለግ መርህ መሰረት፤ የሰላም ንግግሩን ደቡብ አፍሪካ ለማስተናገድ ፍቃደኛ በመሆኗ፤ ሙሳ ፋኪ ማህማት ሀገሪቱን እና ፕሬዝዳንቷን ሲሪል ራማፖሳን አመሰግነዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ሰላምን ለማስፈን ባሳዩት ቁርጠኝነት “ይበልጥ እንደተበረታቱም” የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)