በሃሚድ አወል
ላለፈው አንድ ዓመት በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት ሲሰሩ የቆዩት ዶ/ር በከር ሻሌ፤ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተሾሙ። ዶ/ር በከር በደቡብ ኮሪያ የዶክትሬት ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከተመለሱ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት፤ በፌደራል መስሪያ ቤት ሲሾሙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ዶ/ር በከር ሀገራዊ የስታስቲክስ መረጃ ማዕከል በመሆን የሚያገለግለውን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እንዲመሩ የተሾሙት ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 10፤ 2015 ጀምሮ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አዲሱ ዋና ዳይሬክተር በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተፈረመውን የሹመት ደብዳቤ ከተቀበሉ በኋላ፤ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ጥቅምት 10፤ 2015 በቀድሞ መስሪያ ቤታቸው የስራ ርክክብ አድርገዋል።
ዶ/ር በከር የስራ ርክክቡን ያደረጉት፤ በሚኒስትር ዲኤታነት ሲመሩ የቆዩትን የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን ለተረከቡት ዶ/ር ተሻለ በሬቻ ነው። የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከትላንት በስቲያ ባወጣው መረጃ፤ ተሰናባቹ ሚኒስትር ዲኤታ “እንደ ዘርፍ የተከናወኑ የተቋም ግንባታ እና የሪፎርም ተግባራት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ሲል እውቅና ሰጥቷቸዋል።
ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ወደ ኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የተዛወሩት ዶ/ር በከር፤ በነገው ዕለት በአዲሱ መስሪያ ቤታቸው ይፋዊ የአቀባበል እና የትውውቅ መርሃ ግብር ይደረግላቸዋል። ዶ/ር በከር በአዲሱ የኃላፊነት ቦታቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ የቆየውን አራተኛውን የህዝብ እና ቤት ቆጠራ የማካሄድ ትልቅ የቤት ስራ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።
አራተኛው የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ሊካሄድ የታቀደው ከአምስት ዓመት በፊት በየካቲት 2010 ዓ.ም. ነበር። በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት በየአስር ዓመቱ መካሄድ የነበረበት የህዝብ እና ቤት ቆጠራ፤ ከአራት አመታት በኋላ እስካሁንም አልተካሄደም። በፌደራል መንግስት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝርዝር መሰረት፤ በዘንድሮው ዓመት የህዝብ እና ቤት ቆጠራ የሚካሄድ ከሆነ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 409.6 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተመላክቷል።
ለህዝብ እና ቤት ቆጠራ የሚውለው ገንዝብ ከመንግስት ግምጃ ቤት በሚገኝ ገንዘብ እንዲሸፍን ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጥያቄ መቅረቡ በበጀት ዝርዝሩ ላይ ቢጠቀስም፤ በገንዘብ ሚኒስቴር ተቀባይነት ስለማግኘቱ ግን በግልጽ አልተቀመጠም። የህዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበትን ጊዜ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት እና መረጃ አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ፤ ጉዳዩ የሚመለከተው የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን በመሆኑ መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የህዝብ እና የቤት ቆጠራ ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው በ1999 ዓ.ም ነበር። አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ ውጤቶች የተመዘገቡበት ይህንን የህዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤት በበላይነት ያስፈጸሙት፤ በወቅቱ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጂንሲ በሚል ስያሜ የሚታወቀውን መስሪያ ቤት ይመሩ የነበሩት ወ/ሮ ሳሚያ ዛካሪያ ናቸው።
የኢትዮጵያን ኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ “ወጥ በሆነ እና በታለመለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲሰበሰብ የማድረግ ኃላፊነት” በአዋጅ የተጣለበትን ይህን መስሪያ ለ11 ዓመታት የመሩት ወ/ሮ ሳሚያ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በ2009 ዓ.ም. ነበር። እርሳቸውን የተኩት አቶ ቢራቱ ይገዙ፤ እስካለፈው ሳምንት ድረስ መስሪያ ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ ቆይተዋል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጂንሲ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ተግባራዊ በተደረገው የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዲስ አወቃቀር፤ ስያሜውን ወደ ኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እንዲቀየር ተደርጓል። የስታቲስቲክስ አገልግሎት የሚሰጠውን መስሪያ ቤት የመምራት ኃላፊነት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተረከቡት ዶ/ር በከር፤ ከክልል እስከ ፌደራል ባሉ ተቋማት ለበርካታ ዓመታት የሰሩ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል ከወረዳ እስከ ዞን በአስተዳዳሪነት የሰሩት ዶ/ር በከር፤ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና በህብረት ሥራ ኤጀንሲም በኃላፊነት አገልግለዋል። በ2005 ዓ.ም የአዳማ ከተማን በከንቲባነት መርተዋል። ዶ/ር በከር ወደ በፌደራል ደረጃ የመጀመሪያውን የኃላፊነት ቦታ ያገኙት በቀድሞው የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ነው። በዚህ መስሪያ ቤት በሁለት የተለያዩ ጊዜያት በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት እና በዋና ዳይሬክተርነት ሰርተዋል።
በጥቂት ዓመታት በበርካታ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተሹመው የሰሩት ዶ/ር በከር፤ በቀድሞው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ዴኤታነት አገልግለዋል። ዶ/ር በከር በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ወቅት የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት እንዲመሩ ተደርገው ነበር። ከዚህ ሹመት አንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ዶ/ር በከር የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ደቡብ ኮሪያ አቅንተዋል።
በህዝብ አስተዳደር የጥናት ዘርፍ በነሐሴ 2012 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር በከር፤ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በቀድሞው የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት በአሁኑ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል። በኢንስቲትዩቱ ለአንድ ዓመት የሰሩት ዶ/ር በከር፤ ወደ ስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት ተሹመው የሄዱት ባለፈው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)