የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር “ወደ ተኩስ አቁም ይመራል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ገለጹ

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በደቡብ አፍሪካ የጀመሩት የሰላም ንግግር “ወደ ተኩስ አቁም ይመራል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ተናገሩ። ማህማት ከተጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የሰላም ንግግር ተስፋ እንዳላቸው የገለጹት፤ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በተገናኙበት ወቅት ነው። 

ማህማት እና ብሊንከን ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 17፤ 2015 በካናዳ ኦታዋ ለውይይት ሲገናኙ ከዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳዮቻቸው አንዱ፤ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግር ነበር። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር ያደረጉት ውይይት የተካሄደው “በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሁከትና ግጭት ለማስወገድ የአፍሪካ ህብረት የመሪነት ሚና እየተጫወተ ባለበት ወሳኝ ወቅት” መሆኑን ተናግረዋል። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት ከማህማት ጋር በሰጡት አጭር መግለጫ፤ ሁለት አመት ገደማ ለዘለቀው ጦርነት የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ ስለሚያደርጉት “የጋራ ጥረት ከሊቀመንበሩ ለመስማት ጓጉቻለሁ” ብለው ነበር። መግለጫውን ከሰጡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ደግሞ “በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን ሊቀመንበሩ ፋኪ እና የአፍሪካ ህብረት ወሳኝ ናቸው” ብለዋል። 

የአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ንግግር የተጀመረው ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 15፤ 2015 ሲሆን አሜሪካ በታዛቢነት ትሳተፍበታለች። ከአሜሪካ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ተወካዮች “በታዛቢነት” ይሳተፉበታል የተባለው የሰላም ንግግር፤ በመጪው እሁድ እንደሚጠናቀቅ የደቡብ አፍሪካ መንግስት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)