የኢትዮጵያ መንግስት “በኢትዮጵያ ላይ ያልተረጋገጡ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች” ያቀርባሉ ካላቸው ሀገራት እና አንዳንድ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ እንዲያጤን መገደዱን አስታወቀ። በተለያዩ የምዕራባውያን አካላት አማካኝነት “በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የሐሰት ስም ማጥፋቶችን” ፈጽሞ እንደማይታገስም ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ያስታወቀው በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል ዛሬ አርብ ጥቅምት 18፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። መግለጫው “ኃላፊነት የጎደላቸው” ሲል የጠራቸው አካላት “ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ” ሲባል መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችን እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቅሷል።

እነዚህ አካላት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ክስ የሚያቀርቡት “ፍንጮችን ወይም ተጨባጭ ክስተቶችን መሰረት አድርገው አይደለም” የሚለው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ፤ ውንጀላዎቹ “ ‘የመፈጸም ዕድል አለ’ በሚል ባልተጨበጠ ግምት” ላይ የተመሰረቱ ናቸው ሲል ተችቷል። የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ “በኢትዮጵያ ላይ ተቀነባብሮ እየተለቀቀ ነው” ያለውን ፕሮፖጋንዳ “የተሻለ ስም ያላቸው ተቋማት ሳይቀሩ” ለመቃወም አለመቻላቸው “እጅግ የሚያሳዝን ነው” ብሏል።
አንዳንድ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ የሐሰት ክሶችን “ኢትዮጵያ ለማንበርከክ ሊጠቀሙባቸው ይፈልጋሉ” ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው መግለጫው ወንጅሏል። “ይሄን መሰል አስደንጋጭ ክሶችን አቅርቦ የኢትዮጵያ መንግስትን በማስጨነቅ በሕወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን የመከላከል እርምጃ ለማስቀየስ የሚችሉ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል” ሲል ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፏል።
“አንዳንድ ምዕራባውያን ባለስልጣናት ጭምር ይሄንን የሐሰት ክስ የሚነዙት ኢትዮጵያ ትዕዛዛቸውን አልቀበል ስላለቻቸው መሆኑን በይፋ መናገር ጀምረዋል”
– የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
“አንዳንድ ምዕራባውያን ባለስልጣናት ጭምር ይሄንን የሐሰት ክስ የሚነዙት ኢትዮጵያ ትዕዛዛቸውን አልቀበል ስላለቻቸው መሆኑን በይፋ መናገር ጀምረዋል” ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከስሷል። “ይሄን የመሰሉ የከፉና ሊወገዙ የሚገባቸው ውንጀላዎች፤ ለፖለቲካ ዓላማ መዋላቸው ኃላፊነት የጎደለውና አሳፋሪ ነው” ሲል ነቅፏል።
በኢትዮጵያ ላይ እየቀረቡ ይገኛሉ የተባሉት “አደገኛ ስም ማጥፋቶች” የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በኋላ “ፈጽሞ እንደማይታገስ” የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። “ያልተረጋገጡ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች” ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገራት እና ተቋማት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ግንኙነት መልሶ እንዲያጤን እንደተገደደ መግለጫው ገልጿል። ሆኖም መግለጫው ሀገራቱ እና ተቋማቱ እነማን እንደሆነ በስም ሳይጠቅስ ቀርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)