የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ስደተኞችን የተመለከተ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያካሄድ ነው

በሃሚድ አወል

ሀገራዊ የስታስቲክስ መረጃ ማዕከል በመሆን የሚያገለግለው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ስደተኞችን የተመለከተ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ደህንነት ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያካሄድ ነው። በአምስት ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወነው ይህ ጥናት ከሚቀጥለው ህዳር ወር ጀምሮ እንደሚደረግ አገልግሎቱ አስታውቋል።

የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ደህንነት ጥናቱን ማካሄድ ያስፈለገው፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ “ስደተኞችን ጉዳይ ለመመለስ እና ለቀጣይ ዕቅዶች ግብዓትነት” ለማዋል እንደሆነ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት እና መረጃ አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጥናቱ በዋናነት የሚያተኩረው በአስገዳጅ ሁኔታ ተሰድደው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች ላይ ቢሆንም፤ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎችንም እንደሚያካትት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

ከህዳር 10፤ 2015 ጀምሮ የሚካሄደው ይህ የዳሰሳ ጥናት፤ በአፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚገኙ 21 የስደተኞች መጠለያዎችን ይሸፍናል። ጦርነት እየተካሄደበት በሚገኘው ትግራይ ክልል ሶስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ቢኖሩም፤ “በወቅታዊው ሁኔታ ምክንያት” በጥናቱ አለመካተታቸውን አቶ ሳፊ ተናግረዋል። ከስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውጭ በአዲስ አበባ ከተማ እየኖሩ ያሉ የኤርትራ እና ሶማሊያ ስደተኞች የጥናቱ አካል እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ አክለዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ 70,000 ገደማ ስደተኞች እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ከአንድ ወር በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። በዚሁ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በሚገኙ 24 የስደተኞች ጣቢያዎች ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ብዛት 875,879 ነው። የጋምቤላ ክልል ከአጠቃላይ ስደተኞች 42.7 በመቶውን በማስተናገድ ቀዳሚ ሲሆን፤ የሶማሌ ክልል 249, 934 ስደተኞችን በማስጠለል በሁለተኛነት ይከተላል።  

በኢትዮጵያ ከሚገኙት ስደተኞች ውስጥ ግማሽ ገደማ ያህሉ የደቡብ ሱዳን ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ የUNHCR መረጃ ይጠቁማል። በብዛት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን የያዙት ከሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ ስደተኞች ናቸው። የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት በ288 የቆጠራ ቦታዎች የሚገኙ 3,456 ቤተሰቦች የሚሸፍን እንደሆነ የመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት እና መረጃ አሰባሰብ ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ በሚደረገው በዚህ የዳሰሳ ጥናት 127 ባለሙያዎች መረጃዎችን በመሰብሰብ ይሳተፋሉ ተብሏል። የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለእነዚህ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት መጀመሩን አቶ ሳፊ ጠቁመዋል። የስታቲስቲክስ አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ስደተኞች ላይ ብቻ ያተኮረ ጥናት አለመስራቱን የሚገልጹት አቶ ሳፊ፤ የአሁኑ ጥናት ለፌደራል መንግስት እና ለዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች “ዋና ግብዓት ሆኖ ያገለግላል” ሲሉ ጠቀሜታውን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)