የሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ቆቦ እና ሮቢት አካባቢዎች ከዛሬ ምሽት ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኛሉ ተባለ 

በሃሚድ አወል

ከአላማጣ የማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል የሚያገኙ የአማራ እና የትግራይ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እስከ ነገ ማክሰኞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሰው እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። በደቡባዊ ትግራይ ዞን የምትገኘው የአላማጣ ከተማ ከትላንት ምሽት ጀምሮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘቷን የአገልግሎቱ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

እንደ አቶ መላኩ ገለጻ ከአላማጣ እስከ ቆቦ ያለው የመካከለኛ የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል። “ከአላማጣ ቆቦ ባለው መስመር የዛፍ ቅርንጫፎችን መመንጠርና አገልግሎቱን የማስጀምር ስራ ነው የቀረው” ሲሉ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። 

አቶ መላኩ አክለውም “ከተቻለ እና ይሄ ከተጠናቀቀ ሮቢትን ጨምሮ ቆቦ እና አካባቢው ዛሬ ምሽት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሰው እንዲያገኙ እየሰራን ነው” ብለዋል። በተመሳሳይ ከአላማጣ የማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል የሚያገኙ የሰቆጣ እና የላሊበላ አካባቢዎችም ዛሬ ምሽት ኃይል ያገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአላማጣ እስከ ላሊበላ የተዘረጋው የ66 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር የጥገና ሥራ 90 ከመቶ መጠናቀቁን የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ መላኩ እንዳሉት በኤሌክትሪክ መስመሮቹ ጥገና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሰው የሚያገኙት የአማራ ክልል አካባቢዎች ብቻ አይደሉም።   

“ከተቻለ እና የጀመርናቸው ስራዎች ከተጠናቀቁ እነ ኮረም እና ዋጃም ማምሻውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሰው እንዲያገኙ ነው እየሰራን ያለው” ሲሉ በደቡባዊ ትግራይ ዞን የሚገኙት ከተሞችን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። “ምናልባት [ጥገናው] ዛሬ የማይጠናቀቅ ከሆነ ነገ አገልግሎቱን መልሰው እንዲያገኙ ይደረጋል” ሲሉ አቶ መላኩ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።

የሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ቆቦ እና ሮቢት አካባቢዎች ከዛሬ ምሽት ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያገኙ የተገለጸው፤ የፌደራል መንግስት “ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያስችሉ መሰረታዊ ስራዎችን” እየሰራ እንደሚገኝ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ማስታወቁን ተከትሎ ነው። መንግስት ይህን ያስታወቀው የአላማጣ፣ ኮረም እና ሽሬ ከተሞችን መቆጣጠሩን ይፋ ባደረገበት ወቅት ነበር።

የፌደራሉ መንግስት ከዚህ በተጨማሪ የአማራ እና የትግራይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎችን ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በወቅቱ መግለጹ አይዘነጋም። የመጀመሪያውን መስመር በሰሜን ጎንደር አቅጣጫ በኩል ያለ ሲሆን፤ በአዲ አርቃይ፣ ማይጸምሪ አድርጎ ወደ ሽሬ ከተማ የሚያመራ ነው።

በኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልድያ፣ ቆቦ እና አላማጣ በኩል የሚያልፈው ሁለተኛው መስመር ደግሞ የትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞንን ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጋር የሚያገናኝ ነው። የትግራይ ክልልን በሰሜን ወሎ በኩል ከአማራ ክልል ጋር የሚያገኛነው አውራ ጎዳና ባለፈው ሳምንት ጀምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። 

ሁለት ዓመት ሊሞላው ሶስት ቀናት በቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል መሰረታዊ ሆኑ አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል። የትግራይ አማጽያን በ2013 መጨረሻ ላይ በርካታ ትግራይ ክልል አካባቢዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከአላማጣ የማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል የሚያገኙ የአማራ ክልል አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው ነበር። 

በጦርነቱ ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት “ከፍተኛ ወድመት” እንደደረሰበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አስታውሰዋል። ከአላማጣ እስከ ቆቦ እና ከአላማጣ እስከ ላሊበላ ባሉት መስመሮች 42 የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመሮች “ከጥቅም ውጭ ሆነው ነበር” የሚሉት አቶ መላኩ፤ በተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት “ዝርፊያ” መፈጸሙንም አክለዋል። 

“መሰረተ ልማታችን ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። አጠቃላይ ውድመቱን በገንዘብ ስናሰላው ምን ያህል ነው የሚለውን በቀጣይ አጥንተን የምንመልሰው ነው የሚሆነው” ሲሉ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)