የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ   

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 23፤ 2015 የሰላም ስምምነት በይፋ ተፈራረሙ። ለሁለት ዓመት ጦርነት ሲያካሄዱ የቆዩት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ከስምምነት ላይ የደረሱት፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ ለ10 ቀናት ካደረጉት የሰላም ንግግር በኋላ ነው።

የኢትዮጵያን መንግስት ልዑክ በመምራት የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት ሬድዋን ሁሴን ሲሆኑ፤ ጌታቸው ረዳ ደግሞ የህወሓትን ልዑክ ወክለው ፊርማቸውን በስምምነቱ ላይ አስቀምጠዋል። የልዑካን መሪዎቹ ስምምነቱን በተመለከተ የተዘጋጀውን መግለጫም ተከፋፍለው በንባብ አሰምተዋል። 

ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በደቡብ አፍሪካ ሲያካሄዱት በቆዩት የሰላም ንግግር፤ ግጭት ለማቆም፣ ህግ እና ስርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ፣ አገልግሎቶችን እንደገና ለማስጀመር፣ የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ለማድረስ እንዲሁም ለሰላማዊ ሰዎች በተለይም ለህጻናት፣ ሴቶች እና ተጋላጭ ለሆኑ ሌሎች ቡድኖች ጥበቃ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ እናረጋግጣለን” ሲሉ በመግለጫቸው አጽንኦት የሰጡት ሁለቱ ወገኖች፤ ኢትዮጵያ ያላት “አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ” መሆኑ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል። “በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ እንዲበተኑ ማድረግ እና እንደገና መዋሃድ በሚያስችል ዝርዝር መርሃ ግብር ላይ ተስማምተናል” ሲሉም የተስማሙበትን ሌላ ነጥብ ጠቅሰዋል።  

“በትግራይ ክልል ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ወደነበረበት መመለስን ጨምሮ የሽግግር እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ” ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተፋላሚ ወገኖቹ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት “ሁሉንም አይነት ግጭቶች እና ጠብ አጫሪ ፕሮፖጋንዳዎች ለማቆም” ተሰማምተዋል። ከዚህ በኋላ የሚወጡ መግለጫዎችም “የስምምነቱን አፈጻጸሞች አስመልክቶ ብቻ” እንደሚሆኑ በንባብ በቀረበው መግለጫ ተመላክቷል። 

ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቁት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስምምነቱን እንዲደግፉ እና “ከፋፋይ እና የጥላቻ ድምጾችን እንዲያቆሙ” አሳስበዋል። በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የህዝብ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት እንዲመለሱ እና በግጭቱ የተጎዱ ማህበረሰቦች መሰረተ ልማትን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ተጠቁሟል። 

ከስምምነቱ መፈረም ሰዓታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ስምምነቱን “ታላቅ” ሲሉ ገልጸውታል። አብይ አክለውም “ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከአራት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በጀመርነው የለውጥ መንገዶች ላይ ወደፊት የሚያራምድ ነው” ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው “ስምምነቱ መንግስት ካስቀመጠዉ አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ” መሆኑን በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት አጭር ጹሁፍ ላይ አመልክተዋል። ስምምነቱ “የመላ ህዝባችንን ፍላጎት የሚያሟላ፣ ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ እና የትግራይን ህዝብ መሠረታዊ ችግሮችን የሚፈታ ነው” ሲሉም ዶ/ር ለገሰ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)