በትግራይ ክልል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር መሆኑን የተደራዳሪ ልዑካን መሪዎች ተናገሩ 

በትግራይ ክልል የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሚሆን የኢትዮጵያ እና የህወሓት ተደራዳሪ ልዑካንን የሚመሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። ሁለቱ የልዑካን መሪዎች ይህን ያሉት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ አማጽያን የጦር አዛዦች ዛሬ ሰኞ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ተገናኝተው ድርድር ከመጀመራቸው በፊት ባደረጉት ንግግር ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን በዚሁ ንግግራቸው “የቴሌኮም፣ የኢነርጂ እና የባንክ አገልግሎቶችን መልሰን ማገናኘት አለብን። ከዚያ በፊት [ግን] ሰዎቻችን በቅድሚያ ምግብ እና መድኃኒት ይፈልጋሉ። ይህን ለማፋጠን እየሞከርን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ሬድዋን ክልሎችን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች “በባለፉ ጉዳዮች ከመዘፈቅ ይልቅ” ተስፋ እንዲፈነጥቁ እና መጪውን ጊዜ በጸጋ እንዲቀበሉ መንግስታቸው እያበረታታ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ህወሓትን በመወከል የፈረሙት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ “በስምምነታችን የተካተቱ ብዙ መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ” ብለዋል። ከእነዚህ ተግባራት መካከል የአገልግሎቶች መጀመር አንዱ መሆኑንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። የአገልግሎቶቹ ቁጥር ከፍ ሲል በተደራዳሪ ወገኖች መካከል የሚኖረው “መተማመን እና ግንኙነት አብሮ እንደሚጨምር”፤ “በሰዎች አዕምሮ ውስጥም ተስፋ እንደሚዘራ” የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ “ለማስፈን እየሞከርን ያለውን ሰላም የበለጠ ያጠናክራል” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና በትግራይ ኃይሎች አዛዥ የሚመሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ በአካል ተገኝተው ንግግር ሊጀምሩ ሲዘጋጁ ባሰሙት ንግግር፤ “የገባነውን ቃል ለማክበር ቁርጠኛ ነን” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ከፍተኛ የጦር አዛዦች ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 28፤ 2015 በናይሮቢ ከተማ በአካል የተገናኙት፤ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ከትላንት በስቲያ በስልክ መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው።

የዛሬው ስብሰባ የተጠራው በደቡብ አፍሪካ በተደረሰበት የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 6 መሰረት፤ የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የጦር አዛዦች ስምምነቱ በተፈረመ በአምስት ቀናት ውስጥ ተገናኝተው በዝርዝር ጉዳዮች እና በአተገባበር ላይ ይወያያሉ። የጦር አዛዦቹ ከሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከል በመሬት ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይከናወናል የተባለው የህወሓት ተዋጊዎች “ትጥቅ ማስፍታት” ይገኝበታል። 

ከዚህ በተጨማሪ የዛሬው ስብሰባ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ በአፋጣኝ ማድረስ እና የተቋረጡ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመመለስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ይቀርብበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በመግለጫው አመልክቷል። የዛሬውን የጦር አዛዦቹን ስብሰባ በዋነኛነት የማመቻቸት ሚና የሚጫወቱት የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሲሆኑ አብረዋቸው የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፑምዚ ለምላምቦ እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ሶስቱ የቀድሞ መሪዎች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ለ10 ቀናት በተካሄደው የሰላም ንግግር ወቅትም ተመሳሳይ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)