የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፤ በ4 ቢሊዮን ብር ወጪ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው   

በሃሚድ አወል

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፤ በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ 1,520 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሊገነባ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ ጎፋ አካባቢ ለሚያስገነባቸው ለእነዚህ መኖሪያ ቤቶች የሚውለውን ወጪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር የማግኘት ዕቅድ እንዳለው ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ዕቅዱን ይፋ ያደረገው፤ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትላንት ሰኞ ጥቅምት 28 ባቀረበበት ወቅት ነው። የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለብርሃን ዜና ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ እንዳሉት፤ “የጎፋ ፕሮጀክት” የዲዛይን እና የመሬት ዝግጅት ስራ ተጠናቅቆ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ተገኝቷል። 

በሶስት ሄክታር መሬት ላይ የሚገነቡት እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፤ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ቤት ፈላጊዎች በኪራይ እንደሚቀርቡ በኮርፖሬሽኑ የቤቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ሚኪያስ ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከባለ አንድ እስከ ባለ ሶስት መኝታ ቤት ያሉት እነዚህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው የሚጠናቀቀው ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነም ምክትል ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፤ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶችን የመገንባት፣ የማስገንባት፣ የማከራየት እና የመሸጥ እንዲሁም የፌደራል መንግስት የያዛቸውን ቤቶች እና ይዞታዎች የማስተዳደር ስልጣን ያለው ነው። ኮርፖሬሽኑ ከስድስት ዓመት ገደማ በፊት በ2009 ዓ.ም በወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በአዲስ መልክ ሲቋቋም የተፈቀደለት ካፒታል 33.1 ቢሊዮን ብር ነበር። 

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለ“ጎፋ ፕሮጀክት” ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈልግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ኃይለብርሃን ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ባስመረቀው የገርጂ የመኖሪያ መንደርን ባስገነባበት ወቅት ከኢትዮጵያ ንግድ በንክ ጋር በጋር መስራቱን ያስታወሱት ምክትል ስራ አስፈጻሚው፤ ለ“ጎፋ ፕሮጀክት” የሚያስፈልገውን ገንዘብም ከባንኩ በብድር ለማግኘት ማቀዱን አስታውቀዋል።

“2010 አካባቢ ‘እናንተ ፕሮጀክት አዘጋጁ፤ ገንዘብ ከመንግስት ይቀርባል። ገንዘብ issue አይደለም’ ተብሎ ነበር” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ የተናገሩት አቶ ኃይለብርሃን፤ አሁን ግን ተቋማቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ከባንኮች ጋር የመነጋገር አካሄድን እንደሚከተል ጠቁመዋል። ለ“ጎፋ ፕሮጀክት” የሚውል ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማግኘትም፤ “በመንግስት ድጋፍ ውይይት እንዲደረግ አጀንዳ አስይዘናል” ሲሉም ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ አብራርተዋል።  

መንግስታዊው የልማት ድርጅት ለ“ጎፋ ፕሮጀክት” ግንባታው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያገኘውን ብድር “በምን ያህል ጊዜ ይመልሳል?” የሚል ጥያቄ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የቀረበላቸው አቶ ሚኪያስ፤ “የአዋጭነት ጥናቱን አይተን፤ [ገንዘቡን] በምን ያህል ጊዜ መመለስ ይቻላል የሚለውን በኋላ የምናውቀው ይሆናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱን አዋጭነት በተመለከተ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እያስጠና መሆኑንም ገልጸዋል።  

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለአዲሱ ግዙፍ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በራሱ ለመሸፈን ቢሞክር ሊቸገር እንደሚችል ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል። የፋይናንስ ችግር ለ“ጎፋ ፕሮጀክት” ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የኮርፖሬሽኑ ስጋት መሆኑም ለቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል። አቶ ኃይለብርሃን “በፋይናንስ ዙሪያ ብዙ ምልልሶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አጋርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)