የቀድሞው የ“ኢንሳ” ዋና ዳይሬክተር የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት የታች ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሾሙ

በሃሚድ አወል

የቀድሞው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት የታች ዋና ጸሐፊ (Under-Secretary-General) ሆነው ተሾሙ። የቀድሞው የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ሹመቱ የተሰጣቸው በድርጅቱ ዋና ጸሀፊ መንሱር ቢን ሙሳላም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለድርጅቱ በጻፉት ደብዳቤ የመንግስታቸውን ይሁንታ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል።  

ሚዛናዊና አካታች ትምህርትን በማስተዋወቅ ተገቢ፣ ትክክለኛ እና የበለጸገ ማህበራዊ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጽኦ የማድረግ አላማ ያለው ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት የተመሰረተው ከሶስት ዓመት በፊት ጥር 2012 ዓ.ም ነው። ድርጅቱን የመሰረቱት በአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን፣ እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና የፓሲፊክ ደሴት የሚገኙ 38 ሀገራት ናቸው።

ኢትዮጵያ የድርጅቱን መተዳደሪያ ቻርተር የፈረመችው በ2013 የካቲት ወር ላይ ነበር። መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ጀኔቫ ከተማ ያደረገውን ይህን የበይነ መንግስታት ድርጅት በዋና ጸሀፊነት የሚመሩት የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያላቸው መንሱር ቢን ሙሳላም ናቸው። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ሹመቴን Under-Secretary-General እንዲሆኑ ከመረጧቸው በኋላ፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ይሁንታ ለማግኘት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሰኔ ወር ደብዳቤ መጻፋቸው ተነግሯል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጻፉት የምላሽ ደብዳቤ መንግስታቸው ለሹመቱ ይሁንታ እንደሚሰጥ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፤ ካለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ የቀድሞው የ“ኢንሳ” ዋና ዳይሬክተር የዓለም አቀፉ ድርጅት Under-Secretary-General ሆነው በይፋ መሾማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ዶ/ር ሹመቴ ለዓለም አቀፉ ድርጅት የታች ዋና ጸሐፊነት የታጩት፤ በ“ኢንሳ” ከነበራቸው ኃላፊነት ሳይነሱ በፊት እንደነበርም አስረድተዋል።

“ከዚያ ኃላፊነት ወደዚህ እንደምመጣ ቀድሞ ይታወቃል። ለዚያ ተብሎ ነው ቀድሞ እንድወጣ የተደረገው” ሲሉ በዓለም አቀፍ የተሰጣቸው ሹመት አስቀድሞ የታወቀ እንደነበር አብራርተዋል። ዶ/ር ሹመቴ ከጥር 2012 ጀምሮ ይዘውት የቆዩትን የ“ኢንሳ” ዋና ዳይሬክተርነት ቦታ ለምክትላቸው አቶ ሰለሞን ሶካ ያስረከቡት ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር። የቀድሞው የ“ኢንሳ” ኃላፊ ስልጣናቸውን ካስረከቡ በኋላ የነበሩትን ሶስት ወራት ያሳለፉት፤ አዲሱን ስራቸውን ለመረከብ “የዝግጅት ስራ” በመስራት እንደነበር ተናግረዋል። 

ዶ/ር ሹመቴ የ“ኢንሳ” ዋና ዳይሬክተር ከመሆናቸው በፊት ለስምንት ወራት ያህል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ሹመቴ፤ በፌደራል መስሪያ ቤት የመጀመሪያ ሹመታቸውን ያገኙት በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነበር። በዶ/ር አብይ አህመድ ይመራ በነበረው በዚህ መስሪያ ቤት የአካዳሚክ እና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ሹመቴ፤ በስተኋላ በተቋሙ የሚኒስትር ዴኤታ የኃላፊነት ቦታን በመያዝ ሰርተዋል።

ዶ/ር ሹመቴን የታች ዋና ጸሐፊ አድርጎ የሾመው ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት፤ ዋና መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት የተደረገውን ይህን ስምምነት የፈረሙት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ መንሱር ቢን ሙሳላም እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ተስፋዬ ይልማ ናቸው።

የትምህርት ትብብር ድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ የማድረግ ዕቅዱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስታወቀው፤ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ነበር። ዋና ጸሐፊው በዚሁ ጉብኝታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በአካል ተገኛኝተው ተወያይተው ነበር። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰላሳ ስምንት ሀገራትን ያቀፈው የትምህርት ትብብር ድርጅት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና መስሪያ ቤቱን እስከሚገነባ ድረስ ለጊዜያዊ ቢሮ የሚሆነው አንድ ህንጻ ቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ እንደተሰጠው አቶ ሹመቴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ የሚውል 6.5 ሄክታር መሬት በአዲሱ ገበያ አካባቢ እንደሰጠም አዲሱ የድርጅቱ የታች ዋና ጸሐፊ አክለዋል። 

በጅቡቲ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ከሶስት ዓመት በፊት የተመሰረተው የትምህርት ትብብር ድርጅት፤ ዓመታዊ በጀቱን ከአባል ሀገራት እና ከተባባሪ አባላት የሚሰበስብ ነው። ድርጅቱ ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች በስጦታ እና በኑዛዜ እንዲሁም በቀጥታ ከመንግስት፣ ከህዝብ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጥ እርዳታ ሊቀበል እንደሚችል በመተዳደሪያ ቻርተሩ ላይ ሰፍሯል። የትምህርት ትብብር ድርጅቱ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት እና ከግለሰቦች የሚሰጠው ስጦታ ከአጠቃላይ በጀቱ ከ10 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት በቻርተሩ ላይ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ በተወሰኑ አገላለጾች ላይ ከቆይታ በኋላ ማስተካከያ ተደርጓል]