በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለዜጎች “በጣም ትልቅ አደጋ እና ስጋት” እየፈጠሩ ያሉት “የታጠቁ ኃይሎች” መሆናቸውን የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ። ችግሩን ለመፍታት የሰላም ሚኒስቴር ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከህግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው። በዛሬው የፓርላማ ውሎ ጥያቄዎችን ካቀረቡ የቋሚ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሞጋ አባቡልጉ፤ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ ኢሉባቡር እና ሌሎችም አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች “በስፋት እየተንቀሳቀሱ” መሆኑን አንስተዋል።
“ህዝቡ ከፍተኛ ስቃይ እያየ ነው። የሰው ህይወት እየጠፋ ነው። ንብረት እየጠፋ ነው። ከፍተኛ የሆነ ግጭት ነው ያለው። የብሔር ግጭት አለ። ሌሎችም ችግሮች እየታዩ ስለሆነ፤ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እና ህዝቡ በሰላም እንዲኖር የሰላም ሚኒስቴር ድርሻ ምን ይሆናል?” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ጥያቄ አቅርበዋል። የሰላም ሚኒስቴር ይህን ችግር ለመፍታት ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር የሚሰራቸው ስራዎችን የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች እንዲያስረዱ በአቶ ሞጋ ተጠይቀዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በ“ሸኔ” እና በሀገሪቱ ነፍጥ አንግበው በሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂዎች ምክንያት “በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች አሉ” ሲሉ የጠያቂውን ገለጻ አጠናክረዋል። ታጣቂዎቹ በምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አካባቢዎች በዋነኛነት እንደሚንቀሳቀሱ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ “እነኚህ አካላት ለዜጎች ደህንነት ትልቅ ስጋት ናቸው” በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት አስረድተዋል።
“እነዚህ ታጣቂዎች ምን የፖለቲካ ፍላጎት እንዳላቸው ብዙ ግልጽ አይደለም። ምክንያቱም ንጹሃንን በመግደል የሚመጣ የፖለቲካ ድል በፍጹም ሊታሰብ የሚችል እንዳልሆነ የታወቀ ነገር ነው። ግን እየሰሩ ያሉት በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ በመፈጸም፣ ጅምላ ጭፈጨፋዎችን ማካሄድ የመሳሰሉትን ስራዎች ነው” ሲሉም በታጣቂዎች “በርካታ እና አሳዛኝ ጉዳቶች” መድረሳቸውን ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂዎች የደቀኑት ስጋት “አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተፈታም” ያሉት የሰላም ሚኒስትሩ፤ መንግስት ችግሩን ለመፍታት “ትኩረት ሰጥቶ” በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት በሰላም ሚኒስቴር ደረጃ ብቻ ሳይወሰን፤ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከህግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ብናልፍ አብራርተዋል።

“አሁንም ቢሆን የመንግስት ፍላጎት ነገሮችን በሰላም እየቋጩ የመሄድ [ነው]። ግጭት እና ሞት የሚያመጣው ትርፍ የለም። በሰላም ግን ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን በሚለው መርህ ነው ለመስራት እየሞከርን ያለነው። ይሄ ውጤት ባልመጣበት ጊዜ ግን የግድ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የ’ሚሊተሪ ኦፕሬሽኖች’ እና የተለያዩ የህግ ማስከበር ስራዎች እየተካሄዱ ነው ያሉት” ሲሉ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን የሰላም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት “በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ በጣም ሰፋፊ የህግ ማስከበር ስራዎችን” ባለፈው ዓመት መስራቱን በማብራሪያቸው ያስታወሱት አቶ ብናልፍ፤ በእነዚህ ስራዎች “ብዙ ውጤት” መምጣቱን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። የሰላም ሚኒስትሩ “በጽንፈኝነት ያሉ እና ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን የሚፈልጉ” ያሏቸው ኃይሎች፤ “ከተግባራቸው እንዲወጡ መደረጉን” ለዚህ በምሳሌነት አንስተዋል።
“በህግ ማስከበር ዘመቻው የምንፈታቸውን ችግሮች እየፈታን፣ በወታደራዊ ‘ኦፕሬሽኖች’ የሚሰሩ ስራዎችን እየሰራን፤ አሁን ያለውን በዜጎች ላይ የሚያንዣብበውን አደጋ በዘላቂነት ለመፍታት እና ለማስተካከል ዘርፈ ብዙ የሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት”
አቶ ብናልፍ አንዷለም፤ የሰላም ሚኒስትር
እነዚህ ኃይሎች “ጥያቄም ካላቸው በሰላማዊ መንገድ ተደራድረው ችግራቸውን እንዲፈቱ ለማድረግ የህግ ማስከበር ስራ ተሰርተዋል። ብዙ ውጤትም አምጥተዋል” ብለዋል ሚኒስትሩ። ይህም ሆኖ ግን “ገና ያልተቋጩ፤ አሁንም ድረስ የዜጎች ስጋት ያለባቸው ብዙ አካባቢዎች” መኖራቸውን አቶ ብናልፍ አምነዋል።
“በህግ ማስከበር ዘመቻው የምንፈታቸውን ችግሮች እየፈታን፣ በወታደራዊ ‘ኦፕሬሽኖች’ የሚሰሩ ስራዎችን እየሰራን፣ አሁን ያለውን በዜጎች ላይ የሚያንዣብበውን አደጋ በዘላቂነት ለመፍታት እና ለማስተካከል ዘርፈ ብዙ የሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት። ይሄንን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል” ሲሉም የሰላም ሚኒስትሩ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)