የአንጋፋው “የኢትዮጵያ ፖስታ” አዳዲስ ውጥኖች  

የ128 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፤ የመንግስትን የልማት ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የፖስታ አገልግሎቶችን የማቋቋም እና የማስፋፋት ኃላፊነት ያለበት መንግስታዊ ተቋም ነው። በ2001 ዓ.ም. በተሻሻለው የማቋቋሚያ ደንቡ መሰረት፤ ተቋሙ በመንግስት የልማት ድርጅትነት የሚተዳደር ሆኗል።  ከመጋቢት 2013 ዓ.ም. ወዲህ “የኢትዮጵያ ፖስታ” የሚል አዲስ መለያውን ያስተዋወቀው ድርጅቱ፤ በርካታ የማሻሻያ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል። 

እነዚህን የማሻሻያ ስራዎች በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸው፤ ከመጋቢት 2012 ድርጅቱን በዋና ስራ አስፈጻሚነት በመምራት ላይ የሚገኙት ሐና አርዓያስላሴ ናቸው። ከአሜሪካው ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት በህግ ንድፈ ሃሳብ (legal theory) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያያዙት ሐና ወደዚህ ኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በምክትል ስራ አስፈጻሚነት አገልግለዋል። ሐና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም ሰርተዋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በማከናወን ላይ የሚገኛቸው ማሻሻያዎች፤ ድርጅቱን በኤሌክትሮኒክስ ግብይት እና በመሸጋገሪያ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት (transit e – commerce) ዘርፍ መሳተፍ ያስችለዋል። ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት ስለነበረው እንቅስቃሴ፣ ስለጀመራቸው ማሻሻያዎች እና ወደፊት ሊሰማራባቸው ያቀዳቸው ዘርፎች በተመለከተ፤ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ቆይታ አድርጓል። ሙሉ ቃለ ምልልሱ እንደሚከተለው ቀርቧል።


ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ፖስታ

ጥያቄ፡- ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቷል። እርስዎ ይህንን መንግስታዊ ተቋም የመምራት ኃላፊነት ከተረከቡ ወዲህ የታዩ መሻሻሎች ምንድናቸው? 

ሐና አርዓያስላሴ፡- “የኢትዮጵያ ፖስታ” በሀገራችን ካሉ በጣም ቀደምት ከሚባሉ ተቋማት አንደኛው ነው። አሁን መጋቢት [2015] 129ኛ ዓመታችንን እናከብራለን። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በዋናነት በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም ፖስታ እና ሰነዶችን እንዲሁም ዕቃዎችን ማመላለስ ነው ስንሰራ የቆየነው። ባለፉት ዓመታት በተለይም ከፈረንጆቹ 2020 መጨረሻ ጀምሮ አገልግሎቶቻችንን እንደ አዲስ “ሪፎርም” በማድረግ ላይ ብዙ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል። 

ፖስታ ዋና ስራው የሰዎችን ሰነዶች እና ዕቃዎች ተቀብሎ ማድረስ ስለሆነ ከፍተኛ እምነትን የሚጠይቅ ስራ ነው። ስለዚህ ትልቅ ኃላፊነት ስለተሰጠው ከእድሜውና ካለበት ኃላፊነት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎቶችን መስጠት አለበት። ግን የአገልግሎት ጥራቱ ላይ ከመልዕክት ፍጥነትም ደህንነትም ጋር ተያይዞ ትልቅ የሆነ ቅሬታ ይነሳበት ነበር። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት በዋናነት አተኩረን ስንሰራበት የቆየነው ነገር ባሉን ሶስት ዋና ዋና products ላይ የመልዕክት ደህንነት እና ፍጥነትን ማሻሻል ላይ ነበር።

ከምንሰጣቸው ሶስት አገልግሎቶች ውስጥ ቀዳሚው ደብዳቤ የምንለው፤ ከዜሮ እስከ ሶስት ኪሎ ያሉ በተለይም ሰነዶችን የምናመላልስበት ነው። እንዲሁም ጥቅል የሚባለው እና እስከ 31 ኪሎ ግራም ያሉ ዕቃዎችን የምናመላልስበት ፈጣን ያልሆነው አገልግሎት አለን። እንዲሁም EMS የሚባለው Express Mail Service አለን። ለምሳሌ [እ.ኤ.አ] በ2020 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስለነበር አጠቃላይ የፖስታ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አድሮበት ነበር። 

በዚያ ምክንያት በዓለም አቀፍም፣ በሀገር ውስጥም ያሉ የትራንስፖርት አማራጮች በጣም ውስን በመሆናቸው፤ የመልዕክት ፍጥነት ላይ በጣም ተጽዕኖ ፈጥሮብን ነበር። በፊትም ደግሞ ከውስጥ አሰራራችን ጋር ተያያዞ፤ አብረን ከምንሰራቸው ከሌሎችም ተቋማት ጋር ያለን ቅንጅት ላይ ችግሮች ስለነበሩ፤ መልዕክት በፍጥነት ማድረስ ላይ ችግር ነበር። ስለዚህ እሱን ነገር በዝርዝር እያየን “የቱ ጋር ነው ችግሩ? እንዴት አድርገን እንፍታው?” በሚል ብዙ ለውጦች አድርገናል። 

ለምሳሌ አንዱ ዋና ስራችን ዓለም አቀፍ ንግዶች ናቸው። ከዚህ ሀገር ተነስተው ወደ ሌሎች ሀገራት የሚላኩ መልዕክቶች፤ ከውጭም ደግሞ እንደዚሁ የሚመጡ [አሉ]። እሱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማሻሻያ አድርገናል። አንዱን አገልግሎታችንን ብናይ “EMS” ፈጣን መልዕክት ነው። ለዚያም ነው ደንበኞቻችን “ፕሪምየም” የሚከፍሉበት። በ2013 በጀት ዓመት ላይ ብንመለከት፤ ዓለም አቀፍ ወጪ መልዕክቶቻችን ከየትኛውም ቅርንጫፍ አምጥተን ከሀገር እስኪወጡ ድረስ አራት ቀን እና ከዚያ በላይ ይፈጅብን ነበር። እሱን በአንድ ዓመት አሻሽለነው ከአንድ ቀን ባነሰ፤ በ0.7 ቀን ነው በአማካኝ ዕቃዎችን እያወጣን ያለነው። 

EMSን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ ደብዳቤም ላይ፣ ጥቅልም ላይ ከፍተኛ የሚባል ማሻሻያ አድርገናል። ለእዚህ የአገልግሎት መሻሻል ትልቅ ማሳያ የሚሆነው ነገር በተለይ የዓለም አቀፍ መልዕክቶቻችንን ብዛት በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የ2013 እና የ2014ን ብናነጻጽረው፤ የEMS ዓለም አቀፍ ወጪ መልዕክቶቻችን በሶስት ዕጥፍ ጨምረዋል።

ከፖስታ እና ተያያዥ ስራዎች ውጪ ሌሎችም ስራዎች አሉን። የፋይናንስ አገልግሎት እንሰጣለን፤ ክፍያ እንፈጽማለን እንዲሁም የዕቃ ሽያጭ አገልግሎትም አለን። ስለዚህ የአገልግሎት ማሻሻያው በፖስታው ስራ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ላይ ተመሳሳይ ለውጦችን እያደረግን ቆይተናል። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የድርጅቱ አጠቃላይ የፋይናንስ አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል። በተለይ በ2012 መጨረሻ ላይ የፋይናንስ ቁመናው እጅግ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። አሁን እሱም ተስተካክሎ ገቢያችንም፣ ትርፋችንም ከዓመት አመት እየጨመረ መጥቷል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ፖስታ

ጥያቄ፡- የዓለም የፖስታ ቀን ጥቅምት 3፤ 2015 በተከበረበት ወቅት፤ የተቋሙ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ “የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ወደ ፊት ተግባራዊ በሚደረጉ አማራጮች የመጨረሻ የሎጂስቲክ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር” ተናግረው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ወደ በይነ መረብ የግብይት ስርዓት እንደሚገባ ገልጸዋል። የመጨረሻ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማለት ምን ማለት ነው? አገልግሎቱ ለመጀመር የሚደረገው ዝግጅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ሐና አርዓያስላሴ፡- በአጠቃላይ “የኢትዮጵያ ፖስታ” ብዙ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። በቀጣይ ልንሰራቸው ካሰብናቸው ነገሮች አንዱ ዋና ነገር፤ እስከዛሬም ሰፊ ዝግጅት ስናደርግበት የቆየነው፤ የሀገራችንን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማሳለጥ ላይ ነው። እዚህ ላይ ስንሰራ የቆየነው፤ “የኢትዮጵያ ፖስታ” ለኤሌክትሮኒክስ ግብይት ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት በሚል በተለይ አጠቅላይ የ“ኦፕሬሽን” አሰራራችንን ማስተካከል ነበር። ከመልዕክት ደህንነት እና ፍጥነት ጋር ተያያዞ የሰራናቸው ስራዎች በሙሉ ለኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ትልቅ ግብዓት የሚሆኑ ናቸው።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን የዓለም አቀፍ አካሄድ ስንመለከት፤ ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው የሚገኘው። በሀገራችንም ደግሞ መንግስት የያዘውን የልማት አቅጣጫ ስንመለከት፤ የአስር ዓመት ዕቅዱም ላይ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅዳችንም ላይ የሀገራችን የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስፋት ትልቅ አጀንዳ ነው። የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አምራቹ ምርቱ ላይ አተኩሮ፤ በበይነ መረብ በሚኖረው “ፕላትፎርም” ከገዢዎች ጋር በቀላሉ መገናኘት ይችላል። ከእሱ አኳያ ራሳችንን ስናዘጋጅ ቆይተናል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስንል እንደ “ኢትዮጵያ ፖስታ” የምናስበው በሶስት መልኩ ነው። አንደኛ ዓለም አቀፍ ገቢ መልዕክቶቻችን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ዕቃ ሲያዝ፤ ዕቃው እዚህ ሀገር ውስጥ መጥቶ የሚታደልበትን ሂደት (“last mail delivery” አገልግሎት የምንለውን) ማመቻቸት ማለት ነው። ይሄ አሁንም የምንሰራው ስራ ነው። እኛ ሀገር ከክፍያ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ክፍያ ላይ ብዙ ተሳታፊዎች ባይኖሩም፤ ነገር ግን ክሬዲት ካርድ ያለው ማንኛውም ሰው ቢያዝ እና ዕቃው ቢመጣለት እዚህ ሀገር ውስጥ የሚታደልልት በ“ኢትዮጵያ ፖስታ” አማካኝነት ነው። 

እዚህ ላይ የምናሻሽለው ወይም ቀጣይ እርምጃችን የሚሆነው የቤት ለቤት “ዴሊቨሪን” ማስፋት ነው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለቢዝነሶች ያሉበት ቦታ እናደርሳለን። ግለሰብ ሲሆን ግን ፖስታ ቤት መጥቶ ነው የሚወስደው። ይሄ ውስንነት የሚመነጨው ከሁለት ነገር ነው። 

አንደኛው ሀገራዊ የሆነ የአድራሻ ስርዓት የለንም። መንገዶቻችን እና ቤቶቻችን በአግባቡ ተሰምረው የተሰሩ አለመሆናቸው፤ የትኛውም የ“ዴሊቨሪ” ስራ ላይ ትንሽ ፈታኝ ሁኔታ ይፈጥራል። ሆኖም ግን ያ ነገር እስኪፈታ ድረስ፤ እዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ብዙ የ“ዴሊቨሪ” ኩባንያዎች አሉ። እሱ ውሱንነቱን በከፍተኛ ሁኔታ ያቀልለዋል። 

ሁለተኛው ግን ከእኛ የውስጥ አሰራር ጋር የተያያዘ ነው። ሞተር ሳይክሎቻችንን፣ መኪኖቻችንን መጨመር አለብን። ስለዚህ በዚህ አመት የሞተር ሳይክሎችንም፣ የመኪኖችን ግዢዎች ፈጽመን፤ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚስተናገዱበትን ነገር እየሰራን እንገኛለን። 

ሌላኛው ዓለም አቀፍ የሚወጡ መልዕክቶች ላይ የምንሰራው ስራ ነው። በሀገራችን ያሉ በጣም ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ምርቶች አሉ። ለእነሱ ዓለም አቀፍ የገበያ አማራጭን መፍጠር ማለት ነው። ዓለም አቀፍ አሰራሩ፤ ፖስታ በሁሉም ሀገር ተደራሽነት ያለው ብቸኛው የ“ሎጂስቲክስ ኔትዎርክ” ነው። ይሄ “ኔትዎርክ” ለኤሌክትሮኒክስ ግብይት በጣም ተመራጭ ይሆናል። 

ሀገር ውስጥ ያለ ግብይት ደግሞ አለ። እዚህ ከተለያዩ ከተሞች ወደ ሌሎች የሚደረገው ላይ ለእሱም ከፖስታ የተሻለ “ኔትዎርክ” የለም። ምክንያቱን በርካታ ቅርንጫፎች አሉን። አሁን ወደ 700 አካባቢ ናቸው። ይሄንን በደንብ የመጨመር ዕቅዶች አሉን። ስለዚህ ሀገር ውስጥ ላለው ግብይትም በዚህ መልኩ እንደርሳለን። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ፖስታ

ጥያቄ፡- የበይነ መረብ ግብይትን ማሳለጥ የሚመለከት አንድ ፕሮጀክት ከዓለም ባንክ ጋር እየሰራችሁ ነው። በፕሮጀክቱ ምን አይነት ስራዎች ናቸው የሚሰሩት?

ሐና አርዓያስላሴ፡- ከዓለም ባንክ ጋር ያለው ፕሮጀክታችንን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጋር የምንሰራው ነው። በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት “የመካከለኛ እና አነስተኛ አምራቾችን አጠቃላይ ምርታቸውን መጨመር” የሚል ላለፉት አራት አመታት የቆየ ፕሮጀክት አለ። 

በፕሮጀክቱ እንደ አንድ ውስንነት የታየው የገበያ ተደራሽነት ነው። የ“ኢትዮጵያ ፖስታ የገበያ ተደራሽነት ላይ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይችላል” በሚል ነው ፕሮጀክቱን የተቀላቀልነው። እሱ ላይ ነው እየሰራን ያለነው። አንደኛ ከሌሎች ጋር በአጋርነት “ኦንላይን ፕላትፎርም” እንዲኖር መገንባት ነው። የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ያለ ሰው ምርቱን እዚህ “ፕላትፎርም” ላይ በማስቀመጥ ሲሸጥ፤ እኛ ደግሞ ያንን ወስደን ለተጠቃሚው የምናደርስበትን ሂደት በመስራት ላይ እንገኛለን። 

የ“ኦንላይን ፕላትፎርም” መገንባት ፕሮጀክቱ ካሉት የተለያዩ ክፍሎች አንደኛው ይሄ ነው። አሁን ለምሳሌ ድረ ገጻችን የተወሰነ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ክፍል አለው። በቅርቡ ሙከራ እያደረግንበት ነው። የችርቻሮ ስራ ስለምንሰራ እሱ ላይ ያሉንን ምርቶች እንዲታዩ አድርገናል። እሱን ሰፋ አድርጎ ምርቶቹ የሚታዩበት፣ ክፍያ መፈጸም የሚቻልበት የ“ኦንላይን ፕላትፎርም” መገንባት ነው ስራው። የፕሮጀክቱ ትልቁ አካል የሚሆነው፤ እነዚህን ሁሉ መስራት ነው። 

የ“ኦንላይን ፕላትፎርም” እንዳለ ሆኖ ዕቃዎቹ ግን መንቀሳቀስ እና ለተጠቃሚዎች መድረስ ስላለባቸው የእሱን መሰረተ ልማት መገንባት ደግሞ የፕሮጀክቱ ሌላኛው አካል ነው። በዚህ ውስጥ አንደኛው የማጓጓዛዎችን ቁጥር ማብዛት ነው። እኛም በራሳችን የምንገዛቸው ይኖራሉ። በዚህ ፕሮጀክትም የተያዘ በተለይ የሞተር ሳይክሎች እና “ቫኖች” [አነስተኛ የጭነት መኪኖች] ግዢ እናደርጋለን። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ውስጥም፤ ከአዲስ አበባ ውጭም ዕቃዎችን የምናስቀምጥባቸው የፖስታ ቤት መጋዘኖች ይኖራሉ። 

ጥያቄ፡- የሞተር ሳይክሎች እና ተሽከርካሪዎች ግዢው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ምን ያህል ነው ለመግዛት ያቀዳችሁትስ?

ሐና አርዓያስላሴ፡- በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የምንገዛቸው ሞተር ሳይክሎች አሉ፤ ቫኖች አሉ። እንዲሁም ደግሞ የፖስታ አውቶብሶችም አሉ። የፖስታ አውቶብሶቹ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የምንሰጥባቸው ናቸው። የእነዚህ ነገሮች ዋና ዓላማ፤ ለሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንሰጥበታለን። መልዕክቶቻችንንም በራሳችን ኔትዎርክ እናመላልስባቸዋልን። 

በዚህ ዓመት በዕቅድ የያዝነው ሃምሳ ሞተር ሳይክሎችን ለመግዛት ነው። በአሁኑ ወቅት ከ120 በላይ ሞተር ሳይክሎች አሉን። እነሱን ማብዛት ማለት ነው። አስር “ቫኖች” እንገዛለን፤ አውቶብሶችም እንደፙው። እሱ ላይ ቴክኒካል ዝርዝር መግለጫ አዘጋጅተን፤ በዓለም ባንክ በኩል እስኪጸድቅልን እየጠበቅን ነው። ዓለም ባንክ ሲያጸድቅልን በቀጥታ ወደ ግዢ ነው የምንሄደው።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ፖስታ

ጥያቄ፡- የ“ኢትዮጵያ ፖስታ” ድረ ገጽ ከመገንባት እና እቃዎችን ከማመላለስ ባለፈ በፕሮጀክቱ ላይ ያለው ሚና ምንድን ነው? አዲስ ድረ ገጽ ነው የምትገነቡት ወይስ አሁን ተቋሙ ባለው ላይ ነው ማሻሻያ የምታደርጉት? ክፍያውስ እንዴት ነው የሚፈጸመው?

ሐና አርዓያስላሴ፡- አጠቃላይ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ የእኛ ሚና የሚሆነው ሁለት ነው። አንደኛው “ኦንላይን ፕላትፎርም” መገንባት እና የዕቃዎቹን እንቅስቃሴ ማሳለጥ ነው። ዋናው የእኛ ስራ ዕቃዎቹን ማንቀሳቀስ ስለሆነ፤ አንደኛ ገዢ እና ሻጭን በ“ኦንላይን ፕላትፎርም” እንዲገናኙ ማድረግ እና የክፍያ ስርዓቱን ማስተካከል ነው። ሁለተኛው ደግሞ መሬት ላይ የሚሰሩትን ስራዎች፤ ለምሳሌ ዕቃዎቹ የሚቀመጡበት መጋዘን “ምን አይነት ነው? በምን አይነት መልኩ እና በምን አይነት ሂደት ነው ከመጋዘን ወጥተው ወደ ተጠቃሚው የሚደርሱት?” የሚለውን መስራት ነው። 

ክፍያን በተመለከተ እና ካለን ድረ ገጽ ጋር እንዴት ነው የሚገናኘው የሚለውን ዝርዝር ጉዳዮች እያየናቸው ነው። ለምሳሌ አሁን ያለው ድረ ገጻችን ላይ የተወሰኑ እቃዎችን ለሽያጭ አቅርበናል። በተለይ ከቴምብር ጋር የተያያዙ አብዛኛው የእኛ የራሳችን ምርቶቹ ሆነው በጣም ተጠቃሚ የሚፈልጋቸው ምርቶች አሉን። ስለዚህ እሱን ጨምሮ ሙከራዎች እያደረግን ነው። የክፍያውን ጉዳይ በዝርዝር እያየነው ነው። 

“ኦፕሬሽናል” ስራው ላይ በጣም ጥሩ መሻሻልን ስላደረግን፤ ቀጥሎ የዲጂታል እና የክፍያው ስራ ምን መመስል አለበት የሚለውን እያየነው ነው። ከእያንዳንዱ ባንክ ጋር መስራት ሳያስፈልገን፤ አንድ ሰው ከየትኛውም የባንክ አካውንቱ ሲከፍል እሱን እንዴት ነው “handle” የሚደረገው? የሚለውን እያየን ነው። የሞባይል የክፍያ አማራጮች አሉ፤ ቴሌ ብር አለ፤ ሌሎች አቅራቢዎችም አሉ። ስለዚህ በየትኛውም የክፍያ አማራጭ ቢቀርብ “እንዴት ተደርጎ ወደ ሻጩ ይደርሳል?” የሚሉትን ነገሮች በሙሉ የእዚህ ፕሮጀክት አካል ናቸው። ዝርዝር ጉዳዮችን እያየናቸው ነው።

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ፖስታ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት መግባት ለምን አስፈለገው? ምን ለማግኘት ነው ዘርፉን ለመቀላቀል ያሰባችሁት?

ሐና አርዓያስላሴ፡- የመጀመሪያው ነገር አጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ “ግብይቶች ወደየት እየሄዱ ነው?” የሚለውን ስናይ፤ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ከዓመት ዓመት በጣም እየጨመረ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ሀገርም ከዚህ ነገር ወደ ኋላ መቅረት የለባትም። ወደዚያ ደግሞ መሄዳችን አይቀርም። ስለዚህ ትልቅ የሆነ ማህበራዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የሰዎች የመገበያየት አቅም ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሲመጣ፣ ኢኮኖሚው ሲሻሻል፤ በተወሰነ ዓመታት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት በሀገራችን ትልቁ የግብይት ምንጭ ይሆናል።

ስለዚህ አዝማሚያው እንዲህ ከሆነ፤ እንደ ሀገርም መዘጋጀት አለብን። በዚያ ሂደት ውስጥ ደግሞ “የኢትዮጵያ ፖስታ” ትልቁን ሚና መጫወት አለበት። ምክንያቱም ዕቃዎችን ማመላለስ ላይ የ128 ዓመት ልምድ ስላለን ይሄን ልምዳችንን ትልቅ ግብዓት አድርገን መያዝ እንችላለን። ሎጂስቲክስ ለብዙ ንግዶች ትልቅ ራስ ምታት ነው፤ ምርቱን አመርትኩ፣ አገልግሎቴን ሰራሁ ግን እንዴት አድርጌ ነው ለተጠቃሚ የማደርሰው?’ በሚል። እዚህ ላይ ሰዎች ብዙ መልፋት ሳያስፈልጋቸው፤ የ“ኢትዮጵያ ፖስታ ይሄንን ትልቅ ክፍተት መሙላት ይችላል” በሚል ነው ዋናው የእኛ መነሳሳት።

ሁለተኛው መነሳሳት ደግሞ ገቢ ነው። ከዚህ አገልግሎት ተጨማሪ ከፍተኛ ገቢ እንጠብቃለን። ምክንያቱም አሁን ያለው የዕቃዎች ግብይት በኤሌክትሮኒክስ በሆነ ቁጥር ግዴታ “ዴሊቨሪ” ያስፈልጋል። ይሄም ደግሞ ለእኛ ተጨማሪ ገቢ ያስገኝልናል። ስለዚህ ወደዚህ አገልግሎት እንድንገባ ያደረጉን፤ እነዚህ ሁለት ትልልቅ እሳቤዎች ናቸው። 

ጥያቄ፡- ከዚህ ቀደም በሰጧቸው መግለጫዎች የተቋሙ የፋይናንስ አፈጻጸም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ሲያነሱ ተደምጠዋል። በአሁኑ ወቅት የተቋሙ የፋይናንስ አፈጻጸም ምን ይመስላል? አመታዊ ገቢ እና ትርፉ ምን ያህል ነው? ልትጀምሩት ካቀዳችሁት የኤሌክትሮኒክስ ግብይትስ ምን ያህል ገቢ ትጠብቃላችሁ?

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ፖስታ

ሐና አርዓያስላሴ፡- በአጠቃላይ የፋይናንስ አፈጻጸማችን ባለፉት ሁለት አመታት በጉልህ ተሻሽሏል። ለምሳሌ የ2012 በጀት ዓመትን ስንጨርስ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ላይ ችግሮች ስለነበሩ ወደ 78 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ላይ ነበርን። በ2013 በጀት ዓመት 72 ሚሊዮን ብር ከታክስ በፊት አትርፈናል። ከኪሳራ እንደተነሳ ተቋም ጥሩ አፈጻጸም ነበረን። በ2014 ደግሞ ከታክስ በፊት 187 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት ችለናል። ስለዚህ ከዓመት ዓመት የትርፋችን መጠን ከእጥፍ በላይ ነው እያደገ ያለው፤ ገቢያችንም እንደዚያው።

ለምሳሌ በ2014 በጀት ዓመት ገቢያችን 907 ሚሊዮን ብር ነበር። በያዝነው የ2015 በጀት ዓመት ደግሞ፤ ገቢያችንን 1.2 ቢሊዮን ብር፤ ከታክስ በፊት ያለውን ትርፋችንን ደግሞ 300 ሚሊዮን ብር ለማድረስ እየሰራን ነው። ግባችን፤ ትርፋችንን በየዓመቱ ቢያንስ 60% እና ከዚያ በላይ መጨመር ነው። እንደዚህ ለጠጥ አድርገን የያዝነው፤ አንደኛ ተቋሙ በጣም ታሪካዊ ነው። የተሰማራነውም ብዙ ዘርፎች ላይ ነው። ስለዚህ የሚገባንን ያህል ገቢ ማግኘት እንችላለን።

አሁን በያዝነው በጀት ዓመት፤ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ ዋና ትኩረት አድርገን የምንሰራው። ትኩረታችን “transit e-commerce” ላይ ነው። ይህንን ስራ ጀምረናል። ከቻይና የሚመጡ ዕቃዎችን እዚህ በትነን፤ ወደ ተለያዩ አፍሪካ ሀገራት እናደርሳለን። ከዚህ “transit e-commerce” ከምንለው የምንጠብቀው ገቢ ይኖራል። ሌሎቹ ላይ በዚህ ዓመት ጉልህ የሆነ ገቢ አንጠብቅም። በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ግን አንዱ ትልቁ ገቢያችን ይመጣል ብለን የምንጠብቅ ከኤሌክትሮኒክስ ግብይት ነው።

ጥያቄ፡- በ“transit e-commerce” ምን አይነት አገልግሎቶችን ነው የምትሰጡት?

ሐና አርዓያስላሴ፡- “transit e-commerce” ስንል ሁለት ዓይነት ዋና ዋና ተዋናዮች አሉ። አንደኛው እንደ እኛ አይነት “designated postal operator” የሚባሉት ናቸው። እነርሱ እያንዳንዱን መልዕክት ወደተለያዩ ሀገራት በትነው የሚልኩ ናቸው። “ወደተቀረው የአፍሪካ ክፍል የሚላኩ መልዕክቶችን ሰብሰብ አድርገን እንላክላችሁ፤ እናንተ በትናችሁ ላኩልን” የሚሉ ጥያቄዎች ይመጡልናል ከተለያዩ ሀገራት ይመጡልናል። 

ወደፊት እየጨመረ ይመጣል ብለን የምናስበው አንዱ ትልቁ መጠን፤ ከሌሎች “designated postal operator” የሚመጡ መልዕክቶች ናቸው። ዋና ትኩረታችን የሆነው የተቀረው የአፍሪካ ክፍል ነው። ለዚህ ስራ ዋና ግብዓቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ“ካርጎ ኔትዎርክ” ነው። በተለይ አፍሪካ ውስጥ ጠንካራ “ኔትዎርክ” አለው።

ሁለተኛው አይነት ተዋናዮች “aggregators” የሚባሉት ናቸው። እነዚህ “designated postal operator” ሳይሆኑ፤ ሌሎች ዋና ዋና የድረ ገጽ መገበያያዎች ላይ የሚታዘዙ ነገሮችን ሰብስበው እሱን “handle” የሚያደርጉ ናቸው። አሁን ለጊዜው የጀመርነው ከቻይና የሚመጡ ዕቃዎች ላይ ነው። እያንዳንዱ ዕቃ ከቻይና ተነስቶ ከሚበተን፤ ሰብሰብ ብሎ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ እኛ በትነን ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እናሰራጫለን። ወደፊት ከየትኛውም ሀገር ለሚመጡ ዕቃዎች ተመሳሳይ አገልግሎት እንሰጣለን። 

ይሄንን እንደ ሙከራ እንስራው እና እዚህ ላይ ያለንን አፈጻጸም አይተን ተግዳሮቶችን ከፈታን በኋላ፤ ከየትኛውም ዓለም የሚመጡ መልዕክቶችን ወደ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ወደተቀረው ዓለም እናደርሳለን። ለዚህ ደግሞ ያለን አቀማመጥ ምቹ ነው። ስለዚህ ከየትኛውም ሀገር የሚመጡ መልዕክቶችን እና ዕቃዎችን ወደ ሌሎች ሀገራት በትነን እንልካለን እሱ ተጨማሪ ገቢ ይሆናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)