በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች ስብሰባዎች፤ ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ግብዓት የሚያቀርቡበት አሰራር ተግባራዊ መደረግ ጀመረ  

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የዕቅድ እና የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ግብዓት እንዲሰጡ ማድረግ ጀመረ። ምክር ቤቱ በጀመረው አዲስ አሰራር መሰረት፤ ባለድርሻ አካላቱ በአፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ አስተያየት እና ሃሳብ መስጠት የሚችሉ ሲሆን፤ በዕቅዶች ላይም ያላቸውን ትችቶች እና ግብዓቶች የማቅረብ ዕድል ያገኛሉ።

የተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ዘርፎች የተደራጁ 13 ቋሚ ኮሚቴዎች አሉት። ቋሚ ኮሚቴዎቹ በፓርላማው አማካኝነት ለዝርዝር ዕይታ የሚመሩላቸው የህግ ረቂቆችን የመመርመር፤ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ እንዲሁም ህግ ማመንጨት ስልጣን አላቸው። ኮሚቴዎቹ ከዚህ በተጨማሪ በመንግስታዊ አካላት ላይ ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

እነዚህ ኮሚቴዎች እንዲያከናውኑ ከሚጠበቅባቸው የክትትል እና ቁጥጥር ስራዎች አንዱ፤ የዕቅድ እና አፈጻጸም ግምገማ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ መሰረት፤ ቋሚ ኮሚቴዎቹ የመንግስታዊ አካላትን ዓመታዊ ዕቅድ ከተቀበሉ በኋላ የየመስሪያ ቤቶቹን የስራ አፈጻጸም በሚቀርብላቸው ሪፖርት መሰረት በየሩብ ዓመቱ ይገመግማሉ። በዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ አጠቃላይ ሪፖርት ያደምጣሉ። 

በዚህ መልኩ ሪፖርታቸውን ከሚያቀርቡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በእነዚህ ስብሰባዎች እንዲሳተፉ መደረግ የጀመረው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መሆኑን የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በፓርላማ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ፈትሂ ማህዲ፤ በዕቅድ እና አፈጻጸም ግምገማ ላይ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ የተወሰነው በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶ/ር ፈትሂ “በህግ እና ደንቡ መሰረት ባለድርሻ አካላትም መሳተፍ ይችላሉ የሚል የለም። ነገር ግን በተለያዩ መድረኮች ቢሳተፉ የሚል በቃል የተግባባንበት ሁኔታ አለ” ሲሉ የአፈ ጉባኤው ውሳኔ በቃል የተላለፈ መሆኑን አስረድተዋል። የህግ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱም ውሳኔው መተላለፉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ሁለቱ የፓርላማ አባላት የሚመሯቸው ኮሚቴዎች ውሳኔውን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል። ኮሚቴዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጥቅምት 23፤ 2015 የሁለት የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሪፖርቶች ሲያደምጡ ባለድርሻ አካላትን ጋብዘው ነበር። ይህ አዲስ አሰራር በዚህ ሳምንት በተካሄዱ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ቀጥሏል። 

በአስፈጻሚ አካላት ግምገማዎች ላይ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት “ከአስፈጻሚው መስሪያ ቤት ጋር በጣም በቁርኝት የሚሰሩ እና ‘strategic alliance’ የሚባሉ ቁርኝት ያላቸው ናቸው” የሚሉት ዶ/ር ፈትሂ፤ “አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የሚሰሩትን ስራ እና ያሉበትን ሁኔታ ሊያዩ የሚችሉ፣ ሊመሰክሩ የሚችሉ እና አንዳንድ የተወሰኑ መረጃዎችን ሊሰጡ የሚችሉ” መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የህግ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ በበኩላቸው “ባለድርሻ የሆኑ፤ በቅርብ ርቀት ተቋማቱ ስለሚያከናውኑት ስራ መረጃ ያላቸው ተቀራራቢ የሆነ ሙያ ያላቸው ሰዎች ይሳተፋሉ” ሲሉ በግምገማው ላይ የሚሳተፉትን አካላት ማንነት አብራርተዋል። “እነዚህን ተቋማት ማሳተፍ እና ሃሳባቸውን ማድመጥ የበለጠ የተሟላ ስራ እንድንሰራ ስለሚያግዝ [እና] አዲስ አሰራር ለመፍጠርም ጭምር የተጀመረ ነው” ሲሉም አክለዋል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግልጽ በሚያደርጋቸው መደበኛ ስብሰባዎች ላይ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ሌሎች አካላት በተጋባዥ እንግድነት ሲሳተፉ ቆይተዋል። በፓርላማው የአሰራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ መሰረት በምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ተጋባዥ እንግዶችን አቀማመጥ የሚመለከታቸውን በማማከር የሚወስነው አፈ ጉባኤው ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)