ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በመቶ ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈታ 

በሃሚድ አወል

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከሁለት ወራት እስር በኋላ ዛሬ አርብ ህዳር 2፤ 2015 በመቶ ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈታ። ጋዜጠኛው ከእስር የተፈታው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደለትን ዋስትና ካጸና በኋላ ነው። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትላንትናው ዕለት በነበረው የችሎት ውሎ፤ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ቢያጸናም ከዚህ በፊት ለጋዜጠኛው የተፈቀደለትን የ20 ሺህ ብር ዋስትና ወደ መቶ ሺህ ብር ከፍ አድርጎታል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለጎበዜ የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅ ውሳኔ ያሳለፈው ከአንድ ወር ገደማ በፊት መስከረም መጨረሻ ላይ ነበር። 

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው ዐቃቤ ህግ፤ ጎበዜን ጨምሮ ከእርሱ ጋር በአንድ መዝገብ የተከሰሱት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ደራሲ አሳዬ ደርቤ ዋስትና ሊፈቀድላቸው አይገባም በሚል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል። የይግባኝ አቤቱታው የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በክስ መዝገቡ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ በተቀመጡት ጋዜጠኛ መዓዛ እና ደራሲ አሳዬ ላይ የቀረበውን ቅሬታ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቷል። 

ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበውን ቅሬታ ውድቅ ቢያደርግም፤ አንደኛ ተከሳሽ በሆነው ጎበዜ ሲሳይ ላይ የቀረበው ቅሬታ ግን “ያስቀርባል” በሚል ጎበዜ መልስ እንዲሰጥበት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 3፤ 2015 በጽህፈት ቤት በኩል ባስተላለፈው በዚሁ ውሳኔ፤ ለጎበዜ በስር ፍርድ ቤት “የተፈቀደው ዋስትና ለጊዜው እንዲታገድ” በአብላጫ ድምጽ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የእግድ ትዕዛዙን የሰጠው የይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ የጎበዜን ዋስትና በተመለከተ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን አቤቱታ እና የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ አዲሱ አልጋው በጽሁፍ ያቀረቡትን መከራከሪያ መርምሯል። ፍርድ ቤቱ ትላንት በዋለው ችሎት፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ወስኗል።

ፎቶዎች፦ ምስራቅ ተፈራ

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በስር ፍርድ ቤት ተወስኖ ነበረውን የዋስትና ገንዘብ ወደ መቶ ሺህ ብር ያሳደገው የጋዜጠኛውን ገቢ ከጠየቀ በኋላ ነው። ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በጽህፈት ቤት በኩል በተካሄደው ችሎት፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ በባለቤትነት ለሚያስተዳድረው “የአማራ ድምጽ” ለተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን ንግድ ፈቃድ ሲያወጣ 500 ሺህ ብር ማስመዝገቡን ለችሎቱ ገልጾ ነበር። 

ጋዜጠኛ ጎበዜ፤ በአዲስ አበባ ገነት ሆቴል አቅራቢያ ከሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የተፈታው ዛሬ አስራ አንድ ሰዓት ከሩብ ገደማ መሆኑን ጠበቃው አዲሱ አልጋው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጎበዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጷጉሜ ወር ላይ ነበር። 

ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ላይ መስከረም 20፤ 2015 ሶስት ክሶች መስርቶበታል። በጎበዜ ላይ የቀረበው የመጀመሪያው ክስ፤ “በህዝብና እና በሰራዊት መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ እሳቤ እንዲኖር” ሰርቷል፤ “የመንግስት የመከላከል አቅም ላይ ህዝቡ ያለውን አቋም የሚያፈርስ መረጃ አስተላልፏል” የሚል ነው።

ዐቃቤ ሀግ በጎበዜ ላይ ባቀረበው ሁለተኛው ክስ “ትክክል አለመሆኑን እያወቀ የሃሰት ወሬነዝቷል”  ሲል ወንጅሎታል። ጋዜጠኛው የተጠቀሰበት ሶስተኛ ክስ ደግሞ “በውጊያ እንቅስቃሴ ውስጥ የወገን ጦር አሰላለፍ እና ቦታ፤ ለጠላት እና ለህዝቡ አጋርቷል” የሚል ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)