የኢትዮጵያ መንግስት ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች “ወደማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ የሚያደርግ” ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ሊያቋቁም ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 3፤ 2015 ባካሄደው ስብስባ፤ የተሃድሶ ኮሚሽኑን የሚያቋቁም ደንብ ማጽደቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የተሃድሶ ኮሚሽኑንን ለማቋቋም ከውሳኔ ላይ የተደረሰው “በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ በማስፈለጉ” እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዛሬው መግለጫ አስታውቋል። የኮሚሽኑ መቋቋም “በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች” ትጥቃቸውን ከፈቱ በኋላ፤ “በአገሪቱ የልማት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ” እንደሚያስችላቸው ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)