በሃሚድ አወል
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ለእስር ሲዳረጉ የቆዩት የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፤ የክልሉ የህዳሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። አቶ ግራኝ ሹመቱን ያገኙት የሚመሩት ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመ ከሶስት ሳምንት በኋላ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ የተደረገውን ይህን የሰላም ስምምነት ከጉህዴን ሊቀመንበር ጋር የተፈራረሙት፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ናቸው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው በዚህ የስምምነት ሰነድ ላይ፤ ከጉህዴን ታጣቂዎች መካከል “ለሰላሙ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎች” የአመራር ምደባ እንደሚሰጣቸው ሰፍሯል።
ይህ የአመራር ምደባ “የሌሎች ብሔረሰቦችን መብት ሳይነካ” የሚፈጸም እንደሆነም በሰላም ስምምነቱ ተቀምጧል። በዚህ ስምምነት መሰረት ከሹመቱ በተጨማሪ፤ የመንግስት ሰራተኛ የነበሩ ወጣቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደነበሩበት ስራ መደብ ይመለሳሉ። የትምህርት ዝግጅታቸው ከዲፕሎማ በላይ የሆኑ እና ምደባ ያላገኙ ታጣቂዎች እና የንቅናቄው አባላት ደግሞ በቅድሚያ ስራ ምደባ ያገኛሉ።
በሰባት ገጾች በተዘጋጀው በዚህ የስምምነት ሰነድ ላይ ከተቀመጡ ጉዳዮች አንዱ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ማረሚያ ቤቶች ተጠርጥረው የታሰሩ እና የተፈረደባቸው የጉህዴን አባላት “የህግ አሰራሩን ተከትሎ የሚፈቱበት” አካሄድ ነው። የቤኒሻንጉሉ ጉሙዝ ክልል መንግስት የንቅናቄው አባላት እንዲፈቱ ሊያደርግ የሚችለው፤ “በይቅርታ፣ በምህረት ወይም ክስ በማቋረጥ” እንደሆነ በስምምነቱ ሰነዱ ይፋ ተደርጓል።
የዚህ ስምምነት የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሆኑት የጉህዴን ሊቀመንበር አቶ ግራኝ፤ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባለፈው ሳምንት አርብ መቀበላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሹመቱ ቅሬታ እንዳደረባቸው የሚገልጹት አቶ ግራኝ፤ በ“ክልል ደረጃ የግድ ከአራት ያላነሰ የካቢኔ ቦታ” መያዝ ነበረብን ይላሉ።
በክልሉ ካቢኔ ውስጥ ቢያንስ ሁለት የጉህዴን ሰዎች ቦታ ቢያገኙ “ለክርክርም፤ ለሁሉ ነገርም ይመቸናል” ሲሉ ሊቀመንበሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህን የፓርቲያቸውን አቋም ለክልሉ መንግስት ማሳወቃቸውን የሚያነሱት አቶ ግራኝ፤ “ለጊዜው ሌሎች ሹመቶች በካቢኔ እስከሚሰጡ ድረስ ያሁኑ ሹመት ጊዜያዊ ነው” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ፤ የክልሉ መንግስት የሰጠውን ይህን ምላሽ ጉህዴን መቀበሉንም አስረድተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ፤ ለጉህዴን ሊቀመንበር ሹመት መሰጡትን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም፤ የአቶ ግራኝን ቅሬታ በተመለከተ ምላሽ መስጠት የሚችለው የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል። የጉህዴን ሊቀመንበር ያቀረቡትን ቅሬታ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ሌሎች የክልሉ የስራ ኃላፊዎችም፤ ጉዳዩን ወደ ክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሀቅ አብዱልቃድር መርተውታል። አቶ ይስሀቅን ለማግኘት ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ከእርሳቸው ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጉህዴን በምርጫ ቦርድ ከሁለት ዓመት በፊት የተጣለበት የስረዛ ውሳኔ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደተነሳለት ይታወሳል። ምርጫ ቦርድ ጉህዴን እንዲሰረዝ የወሰነው፤ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት “መስፈርቶችን አላሟላም” በሚል ነበር። ቦርዱ ጥቅምት 21፤ 2015 ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ጉህዴን ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በሶስት ወራት ውስጥ አስተካክሎ እንዲያቀርብ የጊዜ ገደብ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)