በአዲስ አበባ በ500 ቢሊዮን ብር “ሳተላይት ሲቲ” እንደሚገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ ከተማ ከ400 እስከ 500 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ “ሳተላይት ሲቲ” እንደሚገነባ ተናገሩ። “ጫካ ሃውስ” የሚል ስያሜ ያለው ይህ ፕሮጀክት አማካኝነት ቢያንስ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 6፤ 2015 በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው። አብይ የ“ጫካ ሃውስ” ፕሮጀክት ጉዳይን ያነሱት፤ ከሰሞኑ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ49 ቢሊዮን ብር ቤተ መንግስት እየገነቡ ነው” በሚል የተሰራጩ ዘገባዎችን በመጥቀስ ነው። 

“ልንገነባ ያሰብንው ‘የጫካ ሃውስ’ ይባላል። ልንገነባ ያሰብንው ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ኩራት የሚሆን ‘ሳተላይት ሲቲ’ ነው። ልንገነባ ያሰብንው የኢትዮጵያን ቤት ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)