የሙስና ወንጀሎችን የተመለከቱ ጥቆማዎች የሚቀርቡባቸው ቢሮዎች እና ስልክ ቁጥሮች መዘጋጀታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ 

በሃሚድ አወል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከ “ሌብነት” ጋር የተያያዙ ጥቆማዎች የሚቀርቡባቸው ቢሮዎች እና የስልክ ቁጥሮች በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሌብነትን” በተመለከተ ሀገራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ዛሬ ማክሰኞ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው “ሌብነት በጣም አታካች ነገር ሆኗል። በተለይ የገጠመንን ሀገራዊ ፈተና፣ የገጠመንን ሀገራዊ ችግር እንደ ዕድል የወሰዱ ሰዎች፤ ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል” ሲሉ ተደምጠዋል። 

በጉዳዩ ላይ በካቢኔ እና በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ውይይት እንደተደረገበት ያነሱት አብይ፤ “ሀገራዊ ኮሚቴ አቋቁመን ጥናት እያጠናን እንገኛለን። በሁለት ሶስት ቀን ውስጥ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል። “ለዚህ ዓላማ ብቻ የተዘጋጁ ቢሮዎች አሉ፤ ስልኮች አሉ። መረጃ፣ ሰነድ በማቀበል፤ ቢያንስ ባናጠፋ እንኳን ሌብነትን አንገት እንድናስደፋ በጋራ እንስራ” ሲሉ ህዝቡ ጥቆማዎችን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ፋይል በእግሩ አይሄድም’ የሚል ቋንቋ፤ common ቋንቋ ነው። ፋይል በእጅ ብቻ ነው የሚሄደው፤ በእግሩ አይሄድም። ሌብነት ልምምዱ ብቻ ሳይሆን እንደ መብት መወሰዱ አደገኛ ነገር ነው” ሲሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል። “ይህን ነገር መፍትሄ ካላበጀን፤ ‘እድገታችንን ይጎዳል’ የሚለውን ማሰብ ጠቃሚ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አብይ ከዚህ ቀደም በፓርላማ ቀርበው ስለዳኞች እና ፍትህ አካላት “ሌብነት” ያደረጉትን ንግግር አስታውሰው፤ ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለፓርላማ አባላቱ አጋርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ገለጻቸው በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ይስተዋላል ያሉትን “ሌብነት”፤ ላለፉት ዓመታት መንግስታቸውን እየፈተነው ካለው “የዋጋ ግሽበት” ጋር አነጻጽረው አቅርበውታል። 

“ባለፈው ‘ሌብነት በስፋት አለ’ ብዬ አንስቼ፤ አንዳንዶች ካለምንም ጭንቀት እና ስጋት ነገርዬውን ለመቃረን ሲፈልጉ ሰምቻለሁ። ዛሬ በደንብ ጠንከር አድርጌ መድገም እፈልጋለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ልክ እንደ inflation፤ ትልቁ ስብራት የፍትህ ስርዓት ነው” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም አሁንም አለመለወጡን አበክረው አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር “አንደኛ ደረጃ ሌቦች፤ ዳኞች ናቸው” ማለታቸው በዳኞች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር። “በፍትህ ስርዓት ውስጥ ዐቃቤ ህግ ሆኖ፣ ፖሊስ ሆኖ ፤ ‘በገንዘብ አልሰራም፣ ቃለ መሐላ ገብቻለሁ፣ ቃሌን ጠብቄያለሁ፣ እምነት አለኝ’ የሚሉ ሰዎች አሉ” ያሉት አብይ፤ እነደዚህ አይነት ባለሙያዎች ባለፈው እርሳቸው ባደረጉት ንግግር አለመከፋታቸውን ገልጸዋል። 

አብይ በዛሬው ንግግራቸውም ዳኞችን በተመለከተ ተመሳሳይ ገለጻ ተጠቅመዋል። “ሌብነት አለ ሲባል ዝም ብሎ ሳይሆን፤ በቴሌግራም ‘ግሩፕ’ ከፍተው ጉቦ የሚቀባበሉ ዳኞች አሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጅለዋል። አርበኛ ለመሆን ደግሞ ‘እንትናን ፈታሁ፤ እንትናን አሰርኩ’ እያሉ የሚቀላቅሏቸው ጨዋታዎች አሉ። እንደዚህ አይነት ቀልድ ጥሩ አይደለም” ሲሉ አብይ በ”ሌብነት” ተዘፍቀዋል ላሏቸው ዳኞች ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል። የፍትህ ስርዓቱ መሻሻል ካለበት “ጊዜው አሁን ነው” ሲሉም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)