በፍርድ ቤት ዋስትና የተፈቀደለት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ሳይፈታ ቀረ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ30 ሺህ ብር ዋስትና “ዛሬውኑ ከእስር እንዲለቀቅ” የሚል ትዕዛዝ ቢሰጥም ሳይፈታ መቅረቱን ቤተሰቦቹ ተናገሩ። ዛሬ ማክሰኞ የተላለፈው ይህ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በመልዕክተኛ በኩል ቢደርሳቸውም፤ ተመስገንን “አንፈታም” ማለታቸውን የጋዜጠኛው ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ከእስር ሲፈታ ለመቀበል ዛሬ ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ማምራቱን የሚናገረው ታሪኩ፤ ወንድሙ ባለመፈታቱ የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎች በቢሯቸው ተገኝቶ ማነጋገሩን ገልጿል። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደደረሳቸው ማረጋገጫ ቢሰጡትም፤ ተመስገንን እንደማይፈቱት እንደነገሩት ታሪኩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል። “‘ደርሶናል፤ አንፈታም’ ነው ያሉት። ምክንያቱን ግን አልነገሩንም” ሲልም አክሏል። 

ጋዜጠኛ ተመስገን 30 ሺህ ብር በማስያዝ በዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ዛሬ ረፋድ ላይ ትዕዛዝ የሰጠው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ነው። ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን ሲፈቅድ፤ ጋዜጠኛው “የተጠየቀውን ገንዘብ አስይዞ ዛሬውኑ ከእስር እንዲለቀቅ” የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛውን ከእስር ያልፈታበትን ምክንያት ለማጣራት፤ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ለፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ጥያቄ አቅርባ ነበር። የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጉዳዩን አጣርተው መረጃ እንደሚሰጡ ቢገልጹልንም፤ ከቆይታ በኋላ ለተደረገላቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ምላሽ አልሰጡም። 

ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍርድ ቤት ዋስትና ሲፈቀድለት የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ባስቻለው ችሎት፤ ተመስገን በ100 ሺህ ብር ዋስትና ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል መወሰኑ ይታወሳል። በዚህ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኘው የፌደራል ዐቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ፤ ለጋዜጠኛው የተፈቀደው ዋስትና ታግዶ ተመስገን ያለፉትን አራት ወራት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለማሳለፍ ተገድዷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)