የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ የመጀመሪያው የመድኃኒት እርዳታ መቐለ መድረሱን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ

አንገብጋቢ የሕክምና አቅርቦቶች የጫኑ ሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች፤ ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 6፤ 2015 መቐለ መድረሳቸውን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) አስታወቀ። በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ የህክምና ግብዓቶች መቐለ ሲደርሱ፤ የዛሬው የመጀመሪያው መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል።

መቐለ የደረሱት ተሽከርካሪዎች፤ በትግራይ ክልል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስቸኳይ ፍላጎት ለመሸፈን የሚረዱ 40 ቶን አስፈላጊ የህክምና ግብዓቶች፣ ድንገተኛ መድኃኒቶች እና የቀዶ ህክምና ቁሳቁሶችን የጫኑ መሆናቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው መግለጫ ያሳያል። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት፤ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች መቐለ ደርሰው መመልከታቸውን በትዊተር ገጻቸው አረጋግጠዋል።  

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑክ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ፤ “ይህን ጭነት ማድረሳችን ትልቅ እፎይታ ነው” ብለዋል። በትግራይ ክልል “የጤና አገልግሎት ከፍተኛ ጫና” ውስጥ እንደ ወደቀ የገለጹት ኃላፊው፤ የህክምና እርዳታ ለሚሹ ነፍስ የሚያድን እንደሚሆንም ጠቅሰዋል። በትግራይ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት ባይሰጡም፤ አሁንም ድረስ ክፍት የሆኑት መሰረታዊ መድኃኒት፣ ቁሳቁስ እና አንገብጋቢ የግብዓቶች እጥረት እንዳለባቸው የዓለም አቀፉ ተቋም መግለጫ ይጠቁማል።

ባለፈው ጥቅምት 23፤ 2015 ግጭት የማቆም ስምምነት የተፈራረሙት ተፈላሚ ወገኖች “የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማመቻቸት” አድርገውታል ያሉት ጥረት ኒኮላስ ቮን አርክስ አድንቀዋል። ሁለቱ ወገኖች ያሳዩት ድጋፍ፤ የእርዳታ አቅርቦቱን በመደበኛ መልኩ ለማድረስ እና መጠኑንም በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር ተስፋ እንዳሳደረበት ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በመግለጫው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)