የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይሎች የፈረሙት ስምምነት ካልተከበረ፤ አሜሪካ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል አንድ የሀገሪቱ ባለስልጣን አስጠነቀቁ

የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች የተፈራረሙት ስምምነት ተግባራዊ ካልሆነ አሜሪካ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተደረጉ ድርድሮችን በቅርብ የተከታተሉ አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን አስጠነቀቁ። ባለስልጣኑ ይህን ያሉት ትላንት ማክሰኞ ህዳር 6፤ 2015 በቴሌኮንፍረንስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ዘለግ ያለ መግለጫ ነው።

ማንነታቸውንም ሆነ ከየት ሆነው መግለጫው እንደሰጡ ከመግለጽ የተቆጠቡት እኚህ ከፍተኛ ባለስልጣን፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፤ የትግራይ ተደራዳሪዎችን ከናይሮቢ ወደ መቐለ ይዘው በተጓዙበት ወቅት ከህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር መገናኘታቸውን ተናግረዋል። ልዩ ልዑኩ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከከፍተኛ የኢትዮጵያ ባስልጣናት መገናኘታቸውን አረጋግጠዋል።

ፎቶ፦ ፋይል

“ሁሉም ይህንን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት እና የፕሪቶሪያው ቋሚ ግጭት ማቆም ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲያመራ ጽኑ ፍላጎታቸውን ደግመው ገልጸዋል” ሲሉ ልዩ ልዑኩ ከአዲስ አበባ እና ከመቐለ ባለስልጣናት አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ አስረድተዋል። ማይክ ሐመር በትላንቱ የአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር ተገናኘተው፤ በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ በተደረሱት ስምምነቶች ላይ አሜሪካ ስለምታደርገው ቀጣይ ድጋፍ መነጋገራቸውን ባለስልጣኑ ጠቁመዋል። 

በትላንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣኑ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ፤ በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት የተመለከተው ይገኝበታል። ሁለቱ ኃይሎች ከትግራይ ለቅቀው የመውጣት አዝማሚያ እያሳዩ ባለመሆኑ፤ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀብ የመጣል አማራጭን ትከተል እንደሁ ለተጠየቁት ባለስልጣኑ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።  

“ስምምነቱ የኤርትራ ወታደሮችን ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በትግራይ የሚገኙ የአማራ ልዩ ኃይሎች እና የአፋር ሚሊሺያ እንዲወጡ ጥሪ ያቀርባል” ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ባለስልጣናት “መውጣታቸውን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ናቸው” ብለዋል። እነዚህ ኃይሎች ከትግራይ ካልወጡ፤ አሜሪካ ስምምነቱ መከበሩን ለማረጋገጥ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ባለስልጣኑ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  

“እንደ ፖሊሲ መሳሪያ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ሁል ጊዜም የማዕቀብ አማራጭ አላት” ያሉት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ይህንን አማራጭ መቼ እና እንዴት ልትጠቀም እንደምትችል አስረድተዋል። ባለስልጣኑ “በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ተዋናዮች ተጠያቂ በማድረግ ረገድ እና ይህ ስምምነት መከበሩን ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ማዕቀብ ለመጣል አናመነታም” ሲሉ አገራቸው ልትወስድ የምትችለውን ጠበቅ ያለ እርምጃ በግልጽ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)