ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈታ

በሃሚድ አወል

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአምስት ወራት እስር በኋላ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 7፤ 2015 ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተፈታ፡፡ተመስገን ከእስር የተፈታው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ መወሰኑን ተከትሎ ነው፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን የተፈታው ዛሬ ስምንት ሰዓት ተኩል ገደማ መሆኑን ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል፡፡ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ የተመስገንን መፈታት ሲጠባበቅ እንደነበር የጠቀሰው ታሪኩ፤ ራሱ ከማረሚያ ቤት ሲወጣ እንዳገኘው ገልጿል፡፡

ትላንት ማክሰኞ ረፋድ ላይ ለተመስገን የ30 ሺህ ብር ዋስትና የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት“ዛሬውኑ ከእስር እንዲለቀቅ” የሚል ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች “አንፈታም” በማለታቸው ሳይለቀቅ መቅረቱን ቤተሰቦቹ ገልጸው ነበር፡፡

ተመስገን በዋስትና ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር ችሎት፤ ጋዜጠኛው ከዚህ በፊት ለዋስትና ያስያዘው 100 ሺህ ብር አሁን ከተፈቀደለት ዋስትና ተቀንሶ ተመላሽ እንዲሆን አዝዞ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)