በሃሚድ አወል
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፤ በደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ምክንያት ሰራተኞቹን በተቋሙ ማቆየት አለመቻሉን አስታወቀ። የመስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ በተቋሙ ዓመታዊ የሰራተኞች ከስራ የመልቀቅ ምጣኔ 12.4 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ኦዲተሯ ይህን የገለጹት ዛሬ ረቡዕ ህዳር 7፤ 2015 የተቋማቸውን የ2015 ዕቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻም ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት ለመንግስት ወጪ አስተዳዳር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው። መሰረት በዚሁ ሪፖርታቸው ባለፈው ሩብ ዓመት ብቻ፤ 21 ሰራተኞች ከመስሪያ ቤታቸው መልቀቃቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል።
መስሪያ ቤቱን ከለቀቁ ሰራተኞች ሶስቱ ብቻ በጡረታ የተገለሉ መሆናቸው የጠቀሱት መሰረት፤ “አብዛኛዎቹ ምክንያታቸው የተሻለ ደመወዝ ነው” ሲሉ ቀሪዎቹ ለስራቸው ከፍ ያለ ክፍያ ወደሚከፍሉ፤ እንደ ባንክ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወዳሉ ተቋማት በየጊዜው እንደሚሄዱ አስረድተዋል። ተቋሙ ሰራተኞቹን ማቆየት አለመቻሉ “ትልቅ ተግዳሮት ነው” ያሉት ዋና ኦዲተሯ፤ “በተለይ ልምድ ያላቸው [ሰራተኞች] እየለቀቁ ነው። ብዙ invest የተደረገባቸው” ሲሉ ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል።
በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ላይ የፋይናንስ፣ የክዋኔ እና ልዩ ልዩ ኦዲቶችን የማካሄድ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት 678 ሰራተኞች አሉት። ተቋሙ በቀረጸው የአምስት አመት ስትራቴጂ መሰረት፤ በተያዘው በጀት ዓመት የሰራተኞቹን ብዛት ወደ 1,013 የማሳደግ ዕቅድ ነበረው።
መስሪያ ቤቱ ይህን ዕቅድ ቢይዝም፤ በሚፈለገው ልክ ሰራተኞች መቅጠር አለመቻሉን መሰረት ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል። “አዲስ ተቀጣሪዎች ከታች ነው የሚያድጉት። አብዛኛው ክፍት ቦታ ያለን መሃል ላይ ነው። መሃል ላይ ያለውን [ለመሙላት] ደግሞ ከታች ያሉት ማደግ አለባቸው” ሲሉ ሰራተኞች መቅጠር ያልቻለበትን ምክንያት ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አብራርተዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፤ የደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ስኬል እንዲስተካከል ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ መሰረት ተናግረዋል። “ጥናት አድርገን ጥያቄያችንን አቅርበናል። የገንዘብ ሚኒስቴር እና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስተያየት እንዲሰጡበት እየተጠበቀ ነው” ሲሉ ሂደቱ ያለበትን ደረጃ ያብራሩት መሰረት፤ “የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ቢመለሱልን፤ ኦዲተሮችን በማቆየት ስራውን በአግባቡ ማስቀጠል ይቻላል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ለሰራተኞች መልቀቅ ከደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶች ይኖሩ እንደው ጥያቄ አቅርበዋል። ከድር እንድሪስ የተባሉ የፓርላማ አባል “በተቋሙ አካባቢ ያለውን የስራ መንፈስ አንዴት ነው የገመገሙት? ምቹ የስራ ሁኔታ ከሌለ ባለሙያ ሊለቅ ይችላል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ሱመያ ደሳለው የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባልም በተመሳሳይ “ሰራተኞች እየለቀቁ ያሉት በጥቅማ ጥቅም ብቻ ነው ወይ ? ተቋሙ ላይ የተለየ የተሰራ ውስጣዊ ዳሰሳ ምንድን ነው?” ሲሉ ዋና ኦዲተሯን ጠይቀዋል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ዋና ኦዲተር መሰረት፤ “የኦዲተር መስሪያ ቤት በራሱ ነጻነት አለው። በሙያው ላይ ማንም ጣልቃ አይገባም። አንዳንዱ ነጻነቱን ብቻ ፈልጎ፤ ደመወዝ እያነሰው የሚቀር አለ” ሲሉ የመስሪያ ቤታቸው የስራ ከባቢ ለሰራተኞች መልቀቅ ምክንያት እንደማይሆን ተናግረዋል።
የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ኦዲተር አበራ ታደሰም በተመሳሳይ “ከእኛ መስሪያ ቤት ሲለቅቁ መጠይቅ አዘጋጅተን ለምን እንደሚለቅቁ [መረጃ] እንሰበስባለን። በሙሉ በደመወዝ ችግር ነው እየለቀቁ ያሉት” ሲሉ ዋና ምክንያቱ ደመወዝ መሆኑን ገልጸዋል። ዋና ኦዲተሯም ሆኑ ምክትል ዋና ኦዲተሩ፤ የተቋሙ ሰራተኞች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ “አሳሳቢ” መሆኑን በማንሳት ፓርላማው ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)