በትግራይ አስቸኳይ ድጋፍ ለመስጠት እና የሚያስፈልጉትን ሰራተኞች ለማሰማራት በመጪዎቹ ቀናት በርካታ የአውሮፕላን በረራዎች ለማድረግ መታቀዱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ የበረራ አገልግሎት እና የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አውሮፕላኖች፤ ትላንት ረቡዕ ህዳር 7፤ 2015 ወደ ሽሬ የሙከራ በረራ አድርገዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሐን ትላንት ምሽት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ለሙከራ ወደ ሽሬ የበረረው አውሮፕላን የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የሚጠቀምበት ነው። የዓለም የምግብ ፕሮግራም፤ የእርዳታ ሰራተኞችን ለማፈራረቅ፣ የነፍስ አድን የህክምና እና የንጥረ ምግብ አቅርቦቶችን ለማጓጓዝ ይቻል ዘንድ፤ የሰዎች እና የጭነት ማጓጓዣ በረራዎች ወደ መቐለ እና ሽሬ በአፋጣኝ መጀመር አለባቸው የሚል አቋም እንዳለው ፋርሐን ገልጸዋል።
WFP በትላንትናው ዕለት ወደ ሽሬ ካደረገው የሙከራ በረራ በተጨማሪ ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ “በጎንደር በኩል ወደ ምዕራብ ትግራይ” መግባታቸውን አስታውቋል። ከ16 ወራት ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስፍራው የተጓዙ ናቸው በተባለላቸው በእነዚህ ተሽከርካሪዎች የተጫነው “አንገብጋቢ የምግብ እርዳታ”፤ በመጪዎቹ ቀናት ለማይጸብሪ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚከፋፈል የWFP የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች የተጓዙበት፤ ከአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ ሽሬ የሚወስደው መንገድ ክፍት እንደሚሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያስታወቀው ባለፈው ጥቅምት 8፤ 2015 ነበር። WFP ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ ተጨማሪ ምግብ፣ ንጥረ ምግብ እና የሕክምና ግብዓቶች ጭነቶች በሁሉም መንገዶች በቅርብ እንደሚጓጓዙ ገልጿል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ባለፈው ነሐሴ ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ ተቋርጦ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፤ የፕሪቶሪያውን ግጭት የማቆም ስምምነት ተግባራዊ የሚያደርግ ሰነድ በናይሮቢ ከተፈረመ በኋላ ማንሰራራት ጀምሯል። የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ የመድኃኒት እርዳታ ወደ ትግራይ በማድረስ ቀዳሚ የሆነው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ነው። አንገብጋቢ የህክምና አቅርቦቶች የጫኑ ሁለት የድርጅቱ የጭነት ተሽከርካሪዎች፤ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ህዳር 6፤ 2015 መቐለ መድረሳቸው ተገልጾ ነበር።
ICRC ለሰብዓዊ ግልጋሎት የመደበው አውሮፕላን ትላንት ባደረገው የመጀመሪያ የሙከራ በረራ፤ በሽሬ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፉን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል። በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑክ ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች እንደገና መጀመራቸው አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ በፍጥነት ወደ ክልሉ ለማድረስ እና አፋጣኝ ድጋፍ የሚያሻቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስቃይ ለማቃለል እንደሚረዳ ተስፋውን ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)