ዘጠኝ ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ፤ ተጨማሪ 13 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተባለ

በሃሚድ አወል

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ8.8 ሚሊዮን የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ፤ ተጨማሪ 13.4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገለጸ። በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ፤ ወደ ትግራይ ክልል በአራት አቅጣጫዎች እርዳታ እየገባ መሆኑንም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው የ2015 ዕቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው። የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ለቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ሪፖርት፤ ተቋሙ እየሰራው ያለውን ዋና ዋና ተግባራት እና ተግዳሮቶች ያካተተ ነው።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ኮሚሽነር ሽፈራው በዚሁ ሪፖርታቸው፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ብዛት 21.2 ሚሊዮን መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። ከእነዚህ ድጋፍ ፈላጊዎች ውስጥ 11 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት የሚደገፉት “በአጋር ድርጅቶች” መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤  9.9 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በመንግስት በኩል እርዳታ እንደሚቀርብላቸው አስረድተዋል።

“በሁለቱም በኩል ያለው ፍላጎት እና የሚቀርበው የሀብት መጠን እኩል አይደለም። ይህም ተደራሽነት ላይ የራሱ ችግር አለው” ሲሉ በመንግስትም ሆነ “በአጋር ድርጅቶች” በኩል ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት የመንግስትን ድጋፍ የሚሹ 8.8 ሚሊዮን “ተረጂዎች” እንደሚኖሩ የጠቆሙት ዶ/ር ሽፈራው፤ “ለዚህ የሚያስፈልግ እጃችን ላይ 6 ቢሊዮን [ብር] አካባቢ አለ” ብለዋል። 

ለተረጂዎቹ ድጋፍ ለማድረግ ተጨማሪ 13.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ይህንን ገንዘብ ለማግኘት “ከሚመለከታቸው ጋር አብረን እየሰራን ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በሚፈለገው መንገድ ሃብት መሰብሰብ አለመቻሉ፤ ተቋሙን እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች መካከል አንደኛው መሆኑን ዶ/ር ሽፈራው በሪፖርታቸው አንስተዋል። 

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሩብ ዓመት ሪፖርት የተነሳው ሌላው ተግዳሮት፤ “የጋሸበ የእርዳታ ጥያቄ መኖር” ነው። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮችም በዶ/ር ሽፈራው ሪፖርት ላይ እንደ ችግር ተጠቅሷል። የጸጥታ ችግሮች እርዳታን በወቅቱ እንዳይደርስ እና እርዳታ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች ድጋፉን እስከ ጣቢያ እንዳያቀርቡ አድርጓቸዋል ተብሏል። 

ኮሚሽነር ሽፈራው ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ የራሳቸውን እና ከህዝብ የተሰበሰቡ ናቸው የተባሉ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል። በህዝብ የቀረቡ ናቸው የተባሉ አብዛኞቹ ጥያቄዎች፤ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን የተመለከቱ ናቸው። 

በፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተዘጀውን ጥያቄ በንባብ ያሰሙት ዶ/ር የሺመብራት መንገሻ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች በተለይም ለትግራይ ክልል የሚቀርቡ አስቸኳይና ሌሎች እርዳታዎችን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ኮሚሽነር ሽፈራው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በአሁኑ ወቅት በአራት መንገዶች ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።  

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

ዶ/ር ሽፈራው እርዳታ እየተጓጓዙባቸው ከሚገኙ መንገዶች አንደኛው የሰመራ – አባዓላ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል። በጎንደር – ሁመራ አድርጎ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው መስመር ደግሞ ሁለተኛው ነው። ይህ መስመር “ሽሬ፣ ሽራሮ፣ አክሱም እና አድዋ ድረስ የሚዘልቅ፤ ወደ ውስጥ የሚገባ” መሆኑን ዶ/ር ሽፈራው በማብራሪያቸው አስረድተዋል። ወደ ትግራይ እርዳታ እየተጓጓዘበት ያለው ሶስተኛው መንገድ የጎንደር፣ አዲ አርቃይ፣ ማይጸብሪ መስመር እንደሆነ ዶ/ር ሽፈራው ገልጸዋል። አራተኛው መስመር ደግሞ ከወልድያ በቆቦ በኩል ወደ አላማጣ እና ኮረም የሚሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል በተጨማሪ አጎራባች በሆኑት የአማራ እና አፋር ክልሎችም በተመሳሳይ እርዳታዎችን እየላከ መሆኑን ዶ/ር ሽፈራው ተናግረዋል። በሶስቱም ክልሎች “አንድ ላይ 1.5 ሚሊዮን የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚሸፍን ድጋፍ ተደርጓል አሁንም እየተደረገ ነው” ብለዋል። “በእነዚህ አካባቢዎች የሚያጋጥመው የስነ ልቦና ቁስል እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ “በዘላቂነት የስነ ልቦና ድጋፍ ሊሰራ እንደሚገባ አስተውለናል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)