በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ፤ የስራ ማቆም እና ከቤት ያለመውጣት አድማ ለሶስተኛ ጊዜ ተደረገ 

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል በሚገኘው የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ፤ ዛሬ አርብ ከንጋት ጀምሮ የስራ ማቆም እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን ሶስት የከተማይቱ ነዋሪዎች እና አንድ የዞኑ ባለስልጣን ገለጹ። በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የተደረገው አድማ፤ ከጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የዛሬው የስራ ማቆም አድማ በማህበራዊ ሚዲያ እና በበራሪ ወረቀት የተጠራ መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። የጉራጌ ዞን ክልል እንዲሆን ከሚቀሰቅሱ አክቲቪስቶች መካከል አንዱ የሆኑ የወልቂጤ ነዋሪ፤ “ማታ በሞተር ወረቀት ተበትኗል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ይህን ተከትሎ ዛሬ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በወልቂጤ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት እንቅስቃሴ መቆሙን ሶስት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በከተማይቱ ያሉ የንግድ መደብሮች፣ የባንክ ቤቶች እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች እስከ እኩለ ቀን ድረስ ዝግ ሆነው መዋላቸውን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል እና የወልቂጤ ከተማ ፖሊሶች “በብዛት” ሲንቀሳቀሱ መመልከታቸውንም ነዋሪዎቹ አክለዋል። 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የጉራጌ ዞን አመራር፤ በወልቂጤ ከተማ የስራ ማቆም እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የአድማው ምክንያት “ከክልልነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ” መሆኑንም እኚሁ የዞን አመራር ተናግረዋል። 

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ፤ የጉራጌ ዞንን በአጎራባች ከሚገኙ አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር “በክላስተር” በአንድ ክልል ለማደራጀት የውሳኔ ሃሳብ ካቀረበ ወዲህ፤ ዞኑ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ የሚቀስቅሱ ድምጾች ጎልተው መደመጥ ጀምረዋል። ከጉራጌ ፖለቲከኞች እና “አክቲቪስቶች” ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው የ“ክላስተር” አደረጃጀት፤ በዞኑ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።

በዚያው በነሐሴ ወር ይህንኑ የ“ክላስተር” አደረጃጀት በመቃወም፤ በወልቂጤ ከተማ የስራ ማቆም እና በቤት ውስጥ የመቃወም አድማ ለሁለት ጊዜያት ተደርጓል። ነሐሴ 3፤ 2014 የተደረገው የመጀመሪያው አድማ ለአንድ ቀን የቆየ ሲሆን፤  ነሐሴ 19 የነበረው ሁለተኛው አድማ ደግሞ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተደረገ ነበር። 

እንደ ዛሬው ሁሉ የከዚህ ቀደሞቹ አድማዎችም አስተባባሪዎቻቸው በግልጽ የማይታወቁ ናቸው። የሶስቱም አድማዎች ጥሪ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል መተላለፉ ሌላው የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ነው። ባለፈው ዓመት መጨረሻ በሁለት ሳምንት ልዩነት የተጠሩት አድማዎች በሰላም የተጠናቀቁ እንደነበር የሚያስታውሱት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች፤ በዛሬው አድማ ግን ወጣቶችን ለመበተን ወደ ሰማይ የሚተኮሱ የጥይት ድምጾች ይሰሙ እንደበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የተኩስ ድምጽ ይበልጥ በርትቶ ይሰማ የነበረው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ በሚገኘው እና “ጉብሬ” በሚባለው የከተማይቱ ክፍል እንደነበር ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የወጡ ወጣቶች፤ በመኪና መንገዶች ላይ ጎማ ሲያቃጥሉ መመልከታቸውንም ነዋሪዎቹ አክለዋል። ወጣቶች ጎማ ወደማቃጠል እና ድንጋይ ወደ መወርወር የገቡት፤ የጸጥታ ኃይሎች ሊበትኗቸው ከሞከሩ በኋላ መሆኑን የዞኑ የስራ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።  

የዛሬውን አድማ በተመለከተ ከጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እና ከወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። አቶ ላጫን ጨምሮ የጉራጌ ዞን ካቢኔ አባላት በዛሬው ዕለት በቡታጅራ ከተማ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የደረሰው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)