የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት፤ በመጪው ቅዳሜ ሊያከብር ነው

በሃሚድ አወል


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በመጪው ቅዳሜ ህዳር 17፤ 2015 ሊያከብር ነው። የምስረታ በዓሉ በክልል ደረጃ በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚከበር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በቦንጋ ከተማ በሚደረገው ክብረ በዓል፤ የፓናል ውይይት እንዲሁም የምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብር የሚካሄድ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል። በፓናል ውይይቱ ላይ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የተሰሩ ጉዳዮች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች የሚነሱ መሆኑን አቶ የሺዋስ አስረድተዋል። በቅዳሜው ዝግጅት፤ “ለክልሉ ምስረታ በጎ አስተዋጽኦ ያደረጉ እና ያገዙ” ለተባሉ ግለሰቦች እና አካላት “ምስጋና እና ዕውቅና” እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

አስራ አንደኛው ክልል በመሆን ፌዴሬሽኑን የተቀላቀለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ በይፋ ምስረታውን ያካሄደው ከአንድ ዓመት በፊት ህዳር 14፤ 2014 ዓ.ም ነበር። በዕለቱ የምስረታ ጉባኤውን ያደረገው የክልሉ ምክር ቤት፤ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩትን ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾን አዲሱን ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ መርጧል። 

የምስረታውን ዕለት አስመልክቶ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ ረቡዕ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የክልሉ ቀጣይ ትኩረት “የህዝቡን አንብጋቢ ጥያቄዎች መመለስ” መሆኑን አስታውቀዋል። መጪው ጊዜ “የሠላም እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ትኩረት የሚያገኙበት” መሆኑንም ዶ/ር ነጋሽ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አመልክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተመሰረተ ወዲህ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ፤ “የጸጥታ ችግር” መሆኑ ባለፈው ነሐሴ ወር በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገልጾ ነበር። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የአዲሱን ክልል የሰባት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለጉባኤው ባቀረቡበት ወቅት፤ በካፋ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት “በወሳኝ ቦታዎች ሰራዊት ለማስገባት” የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀው ነበር። 

ዶ/ር ነጋሽ በዚሁ ጉባኤ በችግርነት ያነሱት ሌላው ጉዳይ፤ ክልሉ ከምስረታው በኋላ ያጋጠመውን የበጀት እጥረት ነው። የበጀት እጥረቱ፤ ክልሉ የአዳዲስ ሰራተኞችን ቅጥር ጭምር እንዲያቆም እንዳደረጉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ ይፋ አድርገው ነበር። አዲሱ ክልል ያለበትን የአቅም ውስንነት ለመገንባት እና ተቋም ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ የበጀት ውስንነት “ማነቆ” ሆኖ እንደያዘው ዶ/ር ነጋሽ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ተናግረው ነበር። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ ከነባሩ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በመውጣት ሁለተኛው ክልል ነው። ከደቡብ ክልል ለመነጠል በተደረገ ህዝበ ውሳኔ፤ የራሱን ክልል በማደራጀት የመጀመሪያው የሆነው የሲዳማ ክልል ነው። ራስን ችሎ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ፤ በደቡብ ክልል ስር በሚገኙ ሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎችም ሲቀርብ ቆይቷል። 

በክልሉ ያሉ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች፤ አዲስ ክልል በጋራ ለመመስረት ያቀረቡት ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህም መሰረት በመጪው ጥር ወር መጨረሻ፤ “ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የሚኖረውን  12ኛ ክልል ለመመስረት የሚያስችል ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)