በሃሚድ አወል
በዳኝነት ስነ ምግባር ላይ ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል 133 የሚሆኑት ውሳኔ አለማግኘታቸውን የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽህፈት ቤት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቀ። ውሳኔዎቹ የዘገዩት በቀረቡት አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ የሚሰጡት አካላት፤ ጉዳዩቹን የሚመለከቱት ከዋና ስራቸው በተደራቢነት በመሆኑ ነው ተብሏል።
የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት የተቋቋመ ነጻ የዳኝነት አካል ሲሆን፤ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞችን መልምሎ ለሹመት የማቅረብ ስልጣን አለው። የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች የሚመሩበትን የሥነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ክሶች የሚታዩበትን የስነ ሥርዓት ደንብ የማውጣት እና የማስፈጸም ስልጣንም ተሰጥቶታል። በፌደራል ዳኞች ላይ የዲስፕሊን ክስ በሚቀርበብት ወቅት ምርመራውን የማካሄድ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ይኸው ጉባኤ ነው።
በጉባኤው ስር የሚቋቋመው ጽህፈት ቤት በፌደራል ዳኞች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመቀበል ለሚመለከተው ኮሚቴ የመምራት ኃላፊነት ተጥሎበታል። አቤቱታዎቹን የሚመረምሩት ኮሚቴዎች የሚያቀርቡትን የውሳኔ ሀሳብ ለጠቅላላ ጉባኤው የሚያቀርበውም ይኸው ጽህፈት ቤት ነው።
ለፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽህፈት ቤት ባለፈው ዓመት እና በዘንድሮ ሶስት ወራት የቀረቡ አቤቱታዎች ብዛት 185 መሆናቸውን በጽህፈት ቤቱ የፌደራል ዳኞች ፍርድ ምርመራ እና የዳኞች ዲስፕሊን ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ገብረጻዲቅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእነዚህ አቤቱታዎች መካከል 52ቱ ለዳኞች ስነ ምግባር እና የዲስፕሊን ኮሚቴ የቀረቡ ሲሆን፤ በ16 አቤቱታዎች ላይ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ እንደሰጠባቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ጉባኤው ውሳኔ ካሳለፈባቸው አቤቱታዎች መካከል፤ ከ2006 ጀምሮ በዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዳኛ ፋንታሁን ደለለውን አስመልክቶ የቀረበው ይገኝበታል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ በሆኑት አቶ ፋንታሁን ላይ የቀረበውን አቤቱታ የመረመረው ጉባኤው፤ “ከባድ የሥነ ምግባር ጥፋት” መፈጸማቸውን በማረጋገጡ ካለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ ከስራ እንዲሰናበቱ ውሳኔ አሳልፏል።
የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት በተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ፤ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ህዳር 13፤ 2015 ለፓርላማ አቅርቧል። የዳኛው የስንብት የውሳኔ ሃሳብ የቀረበለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ጉዳዩ በዝርዝር እንዲታይ ለፓርላማው የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቶታል።
የውሳኔ ሃሳቡን በተመለከተ በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ አስተያየት ከሰጡ የፓርላማ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሳህሉ ድርብሳ፤ ለዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ቀርበው ጉዳያቸው ሳይታይ አመታት ያስቆጠሩት ዳኞች “ከ133 በላይ” መሆናቸውን አንስተዋል። ከስራ እንዲሰናበቱ ከተወሰነባቸው ከአቶ ፋንታሁን ሌላ፤ የሌሎቹ ዳኞች ጉዳይ “ከምን ደረሰ የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት” ሲሉም ተደምጠዋል።

የፌደራል ዳኞች ፍርድ ምርመራ እና የዳኞች ዲስፕሊን ጉዳይ ዳይሬክተር፤ በዚህ አመት ለዳኞች አስተዳደር ጽህፈት ቤት የቀረቡት 91 መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእነዚህ አቤቱታዎች መካከል አብዛኞቹ አቤቱታዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የቀረቡ ናቸው ብለዋል። የአቤቱታዎቹን ይዘት በተመለከተ “አብዛኛው የስነ ስርዓት ህጉን አለመከተል እና የስልጣን ደረጃዎችን አለማወቅ፤ ማዳላት፣ ታማኝነት እና ቅንነትን ማጓደል ፍትሐዊነትን አለመጠበቅ” ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል።
ዳኞች በእነሱ የዳኝነት ስልጣን ወሰን ላይ የማይወድቁትን ጉዳዮች የማየት አጋጣሚ መኖሩን የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፤ የስልጣን ደረጃን አለማወቅ በዲስፕሊን እንደሚያስቀጣ አመልክተዋል። “ከቀረበው ክስ [ዳኛው] ስልጣኑን ማወቅ ነበረበት። ህጉ ስለሚያዝ፤ ህጉን በአግባቡ ማወቅ፤ ጠንቃቃ መሆን አለበት” ሲሉም ከውሳኔው ጀርባ ያለውን አመክንዮ አስረድተዋል።
የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በ16 አቤቱታዎች ላይ ውሳኔ ቢሰጥም ከቀረቡት አቤቱታዎች አንጻር ቁጥሩ አነስተኛ መሆኑን አቶ ሀብታሙ ያነሳሉ። ለዚህም ምክንያቱን ሲያብራሩ “የስነ ምግባር እና የዲስፕሊን ኮሚቴው አባላት ከፍተኛ ስራ ያለባቸው ሰዎች ናቸው። ከዚህ የተነሳ በሳምንት አንድ ጊዜ የምንገናኘው” ይላሉ።
“ ‘በአንድ ጊዜ ያሉትን መዝገቦች ሁሉ የተወሰነ ዘመቻ አድርገን፣ አይተን ወደ ፍጻሜ ማድረስ የምንችለው በምን መልክ ነው?’ የሚለው ላይ እየተነጋገርን ነው”
አቶ ሀብታሙ ገብረጻዲቅ – የፌደራል ዳኞች ፍርድ ምርመራ እና የዳኞች ዲስፕሊን ጉዳይ ዳይሬክተር
የስነ ምግባር እና የዲስፕሊን ኮሚቴው የሚመራው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ነው። ኮሚቴው የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ተወካዮችን በአባልነት የያዘ ነው። ከዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽህፈት ቤት እና ከተወካዮች ምክር ቤት የተወከሉ አባላትም በኮሚቴው ተካትተዋል።
በዳኞች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች በተመለከተ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ለመዘግየታቸው በምክንያትነት የተቀመጠው ሌላው ጉዳይ፤ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ስብሰባውን በወር አንድ ጊዜ ማድረጉ ነው። “ ‘በአንድ ጊዜ ያሉትን መዝገቦች ሁሉ የተወሰነ ዘመቻ አድርገን፣ አይተን ወደ ፍጻሜ ማድረስ የምንችለው በምን መልክ ነው?’ የሚለው ላይ እየተነጋገርን ነው” ሲሉ አፋጣኝ ውሳኔ ለመስጠት በጽህፈት ቤቱ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)