የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ ከደቡብ ክልል ጋር ለሚያደርገው የሀብት ክፍፍል የፌደራል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀ 

በሃሚድ አወል

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከነባሩ ደቡብ ክልል ጋር ለሚያደርገው የሀብት እና ንብረት ክፍፍል፤ የፌደራል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ጠየቁ። ሁለቱ ክልሎች እስካሁን ያደረጉት የሀብት ክፍፍል ከፊሉን ብቻ መሆኑንም ዶ/ር ነጋሽ ገልጸዋል።    

ዶ/ር ነጋሽ ይህን የተናገሩት ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 17፤ 2015፤ በክልሉ አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የአዲሱ ክልል የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ በሆነችው ቦንጋ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ክብረ በዓል ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የብልጽግና ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች  ተገኝተዋል።

ፎቶዎች፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

ክብረ በዓሉን በንግግር የከፈቱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ ከተደረጉ አበይት ክንውኖች መካከል አንዱ የሀብት ክፍፍል መሆኑን ጠቁመዋል። “ከነባሩ ክልል ጋር ያለን የሀብት ክፍፍል በመለየት ዓመታዊ በጀት እና ተሽከርካሪ ክፍፍል አድርገናል” ያሉት ዶ/ር ነጋሽ፤ ሆኖም በደቡብ ክልል የሚገኙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች ክፍፍል ግን እስካሁን እልባት አለማግኘቱን ገልጸዋል። 

“በጋራ ያፈራናቸው ሀብቶች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ክፍፍል እንዲደረግ፤ የፌደራል መንግስት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ በአክብሮት እንጠይቃለን” ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። በደቡብ ክልል ስር በነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በተደረገ ህዝበ ውሳኔ የተቋቋመው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ ይፋዊ የምስረታ በዓሉን ያደረገው ባለፈው ዓመት ህዳር 14፤ 2014 ነበር።

የአዲሱ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በዛሬው ንግግራቸው ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ቢጠቅሱም፤ “አሁንም በርካታ ተግዳሮቶች ተጋርጠውብናል” ሲሉ ክልሉ ድጋፍ የሚያሻው መሆኑን ተናግረዋል። ዶ/ር ነጋሽ ከዘረዘሯቸው ተግዳሮቶች መካከል፤ ክልሉ ያጋጠመው የበጀት ጉድለት በዋነኛነት የሚቀመጥ ነው። 

“የክልሉ በጀት ከነባሩ የደቡብ ክልል የነበረውን ድርሻ ብቻ ይዞ የመጣ እና የግዴታ ወጪዎችን፣ የመሰረተ ልማት ስርጭትን፣ የህዝብ ብዛትን ታሳቢ ያላደረገ የድጎማ በጀት ክፍፍል መርህን ተከትሎ የተከፋፈለ በመሆኑ፤ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ገጥሞናል” ሲሉ ዶ/ር ነጋሽ በንግግራቸውን አመልክተዋል። 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱት ሌላኛው ተግዳሮት፤ በክልሉ ያሉ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተደራሽነት አነስተኛ መሆን ነው። ተቋማቱ “በቁጥርም ይሁን በጥራት ደረጃቸውን የሚያሟሉ አይደሉም” ያሉት ዶ/ር ነጋሽ፤ “ወረዳ ከተሞች ጭምር መብራት የማያገኙበት ሁኔታ ይስተዋላል” ሲሉው በክልሉን ያለው የመሰረተ ልማት ችግር መጠነ ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል። 

ዶ/ር ነጋሽ በንግግራቸው ማሳረጊያ ያነሷቸው ተግዳሮቶች “ጊዜ የማይሰጡ መሆናቸውን” በመጥቀስ፤ “የፌደራል መንግስት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ አይቶ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ” ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። በዛሬው ክብረ በዓል ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ባደረጉት ንግግር “በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ከጎናችሁ እንደምሆን አረጋግጣለሁ” ሲሉ ለምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)